

ዮሐንስ አንበርብር ሪፖርተር ብሔራዊ ባንክ የተወሰደበትን ሕንፃ አስመልሶ የፋይናንስ አካዴሚ ሊከፍት ነው የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ ዋጋ መተመን የሚጀመርበት የጊዜ ማዕቀፍ ማዕቀፍ ላይ ውሳኔ መደረሱ ተሰማ። የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን ከሚገባው ወይም ከመግዛት አቅሙ በላይ በመሆኑ በገበያ ዋጋ እንዲወሰን ተደጋጋሚ ግፊት በኢትዮጵያ ላይ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ በቅርቡ የኢኮኖሚ ሪፎርሙን ለመደገፍ ለኢትዮጵያ በሰጠው 2.9 ቢሊዮን ዶላር ብድር ውስጥም ይህንኑ የብር የውጭ ምንዛሪ ገበያ ሥርዓት የማስተካከል ጉዳይ በቅድመ ሁኔታነት ማያያዙ ይታወቃል። የአሜሪካ የገንዘብ ተቋም (ትሬዠሪ) ኃላፊ ስቲቨን ሙንቺን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በስልክ መወያየታቸውን ጠቁመው፣ ከአንድ ወር በፊት በትውተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክትም የብር ውጭ ምንዛሪ ገበያ ሥርዓቱ ወጥ ሊሆን እንደሚገባ መነጋገራቸውን ገልጸው ነበር። የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ሐሙስ ሐምሌ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. የፋይናንስ ዘርፉን የአሥር ዓመት ዕቅድ ለውይይት ባቀረቡበት ወቅት፣ የውጭ የብር ምንዛሪ ገበያ ሥርዓቱን ማሻሻል የሚገባ እንደሆነ ነገር ግን ተቻኩሎ የሚፈጸም እንዳልሆነ አስታውቀዋል። የብር የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትን መሠረት በማድረግ በገበያ እንዲወሰን ማድረግ ተገቢ ቢሆንም፣ ወደዚህ የገበያ ሥርዓት ለመግባት ጊዜ እንደሚያስፈልገውና በፋይናንስ ዘርፋ የአሥር ዓመት ዕቅድ ትግበራ ወቅት ወደዚህ ሥርዓት ሽግግር እንደሚደረግ ገልጸዋል። በዚህም መሠረት ከሦስት ዓመት በኋላ በገበያ የሚወሰን የብር የውጭ ምንዛሪ ትመና ሥርዓት ሽግግር እንዲደረግ ውሳኔ ላይ መድረሱን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ አስቀድሞ ሌሎች የፋይናንስ ዘርፍ ማሻሻያ ሥርዓቶች እንደሚከናወኑ የገለጹት የብሔራዊ ባንክ ገዥ፣ የካፒታል ማርኬት (የካፒታል ገበያ) እና የሁለተኛ ገበያ (የሰከንደሪ ማርኬት) ሥርዓቶች እንደሚጀመሩ አስታውቀዋል።...