የፒያሳው ኬዎርኮቭ ሕንፃ ~~~~
ይህ ታሪካዊ ሕንፃ በ1900 መጨረሻ ዓመታት በአርመናዊው ነጋዴ በማቲክ ኪቮርኮቭ (Matig Kevorkoff) እንደተገነባ ይነገራል። ሕንፃው ተገንብቶ እንዳለቀም የኬዎርኮፍ ሱቅና ግምጃ ቤት ሆኖ እስከ ጣልያን ወረራ ድረስ አገልግሏል።
ጣልያን አዲስ አበባ በሚያዝያ 1928 ዓ.ም አዲስ አበባ ሲገባ በነበረው ያለመረጋጋት አራዳ በሌቦች ተዘርፋና ተቀጥላ ነበር። በዚያው ምክንያት ቃጠሎውና ዝርፊያውም ለኬዎርኮቭ ደርሶት ባዶ አስቀርቶት ነበር።
ይህ ሕንፃ ሙሉ በሙሉ ነዶ ባዶውን ቢቀርም ጣያኖች (ከአንዳንድ ለውጥ በስተቀር) ግርማውን እንደተጎናጸፈ፣ ቅርሱን እንደጠበቀ ሊያድሱት ችለዋል። ጣልያን ይሄንን ሕንፃ ከኬዎርኮፍ ወርሶ የጣልያን ፋሺስት ዋና መምሪያ
“Casa Littoria” (የኅብረት ቤት) ብሎ ሰይሞ ሲጠቀምበት ቆየ።
በ1933 ዓ.ም ጣልያን ሲወጣ ሕንፃው በመጀመሪያ
“የኢትዮጵያ እርሻ ባንክ እና የንግድ ምክር ቤት ቢሮ” ሆነ።
በመቀጠልም “ኤልያስ ሆቴል” ተብሎ ለበርካታ ዓመታት ቆየ። ከዚያ አቢሲኒያ ባንክ፣ ሮያል ኮሌጅ፣
ካስቴሊ ሬስቶራንት እና ሁለት ቡቲኮችን በማያዝ እያገለገለ ነው።
ሕንፃውን በ1909 ዓ.ም ያሳነጸውና እስከ ጣልያን ወረራ ጊዜ ድረስ ባለቤት የነበረው ማቲክ ኬቮርኮቭ (ኬዎርኮፍ) ማነው?
*ኬዎርኮፍ በ1859 ዓ.ም ኢስታንቡል ውስጥ ተወለደ።
በአርመን ትምህርት ቤት ተምሮ ወደ ግብፅ ተጓዘ። ለአጭር ጊዜ ግብፅ ውስጥ ቆይቶ በ1888 ዓ.ም ወደ ጅቡቲ አመራ።
በጅቡቲ ቆይታውም የፈረንሳይኛ ተናጋሪና ፈረንሳዊ ዜጋ ለመሆን በቃ። ከአጎቱ ጋር በመሆን ከጅቡቲ ወደ ፈረንሳይ ትንባሆ በመላክ ትልቅ ንግድ ጀመሩ። ቀስ እያለ ንግዱን ወደ ሐረር፣ ድሬዳዋና አዲስ አበባ አስፋፋ። ጎራዴ፣ ሰይፍ፣ ጩቤ እና የመሳሰሉትን በ1890ዎቹ ሐረር ያመርት እንደነበር አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ጥይትና መሣሪያም በማስመጣት በአዲስ አበባ ሱቅ ይሸጥ እንደነበር አንዳንድ ደብዳቤዎች ያሳያሉ።
“ይድረስ ከነጋ ድረስ ይገዙ ማቲክ ኬዎርኮፍ መቶ ሳጥን የፉዚግራ ጥይት ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ አምጥቷልና እንዳይከለከል ይሁን።
ግንቦት 4 ቀን 1899 ዓ.ም አዲስ አበባ
በጣልያን ወረራ ዋዜማ ግንቦት 29 1927 ዓ.ም የወጣው ብርሃንና ሰላም ጋዜጣም ይህንኑ ይጠቁማል። (ጋዜጣው ላይ ያለውን ማስታወቂያ ይመልከቱ።) የትንባሆ ንግድም አዋጪ ሆኖ ስላገኘው በአዲስ አበባ ብቸኛ የትንባሆ አስመጪ ሆኖ ንግዱን ተያያዘው። ከዚህም በተጨማሪ ጥጥ፣ ሐር፣ መጠጥ፣ ዘይት፣ ሳሙና፣ የሕንፃ መሣሪያዎች፣ ብትን ጨርቅ፣ ስጋጃ፣ ሰዓትና የመሳሰሉትን አስመጪና ላኪ ሆኖ ይሠራ ነበር። እንዲሁም ኪዎርኮፍ የኮኛክና የተለያዩ መጠጦች ዋንኛ አስመጪ እንደነበር ምንጮች ያሳያሉ።
በ1919 ዓ.ም የወጣው የብርሃንና ሰላም ጋዜጣ የእነዚህን የኮኛክ መጠጦች ማስታወቂያ ይዞ ይወጣ ነበር።
(ምስሉን ይመልከቱ)
ለዚህ ሁሉ ሥራው ይሆን ዘንድ ነበር በአራዳ የሚገኘውን ኬዎርኮፍ ሕንፃ ያሠራው። የኬዎርኮፍ ሕንፃ ከመሠራቱ በፊት
ኬዎርኮፍ አራዳ ውስጥ በሁለት ሌሎች ሱቆች ውስጥ ንግዱን ያካሂድ እንደ ነበር ምንጮች ያሳያሉ። ከደጎል አደባባይ ፊት ለፊት ከአያሌው ሙዚቃ ቤት በስተቀኝ በነበረ (አሁን የፈረሰ) ጥንታዊ ሕንፃ ውስጥ ኬዎርኮፍ ሱቅ እንደ ነበረው ይታያል። ከዚህም በተጨማሪ እስከ 1920ዎቹ የፖስታ ቴሌግራፍና ቴሌፎን ሕንፃ የነበረው
(የአሁኑ ሲኒማ ኢትዮጵያና ትሪያኖን ካፌ) በ1900ዎቹ መጀመሪያ የኬዎርኮፍ ሱቅ እንደነበሩ ምንጮች ይጠቅሳሉ።
ኬዎርኮፍ ከዚህ ሌላ የሚታወቀው በፈረንሳይ ሌጋሴዎን ውስጥ የዲፕሎማሲና የማስተርጎም ሥራዎችን በመሥራት ነበር። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላም የትውልድ ሀገሩ አርሜኒያ ስትመሰረት ብዙ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
በኢትዮጵያ የአርሜንያ ተወካይ እንደ አምባሳደር ተደርጎ ተመርጦ ነበር። ኬዎርኮፍ ከኢትዮጵያ እና ከፈረንሳይ መንግሥት የክብር ኒሻን ተሸላሚ እንደነበርም የወቅቱ ጋዜጦች ዘግበዋል።
በ1919 ዓ.ም ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የአርመን ኮሚኒቲ ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግሏል። ቀደም ብሎም በ1915 ዓ.ም በአርመን ፖለቲካ ልዩነት የተነሳ ሶስት ቦታ ተከፋፍሎ የነበረውን የአርመን ትምህርት ቤቶች በማውሃድ አንድ ዘመናዊ ትምህርት ቤት (National Armenian Kevorkoff School) ብሎ ሰይሞት አቋቁሙ ነበር።
እስካሁንም ይሄ ትምህርት ቤት በአራት ኪሎ አርመን ሰፈር ይገኛል። እንዲሁም የኢትዮጵያ ባንክ (Bank of Abyssinia) ቦርድ አባል እና የሎተሪ ኮሚሽን አማካሪ ሆኖ አገልግሏል።
በጣልያን ወረራ ዋዜማ ኬዎርኮፍና ሌሎች የውጭ ሀገር ዜጋ ነጋዴዎች በአንድነት ግማሽ ሚሊዮን ብር አዋጥተው ለኢትዮጵያ የጦርነት ወጭ ድጋፍ ይሆን ዘንድ ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አበርክተው ነበር። ይህንንም ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ በታህሣሥ 2 1928 ዓ.ም እትሙ ዘግቦታል።
በ1928 ዓ.ም ጣልያን አዲስ አበባ ሲገባ በፈረንሳዊነቱ ምክንያት ንብረቱ በሙሉ “የጠላት ንብረት” ተብሎ እንደተወረሰበት ይነገራል። በዚህም የተነሳ ወደ ፈረንሳይ ተሰዶ በፈረንሳይ ማርሴ ከተማ እንደሞተ ይነገራል።
ታዲያ እሱ ቢያልፍም በአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ ጥሎልን አልፏል።
ምንጭ….
አንድምታ የጥበብ መጽሔት

ተጨማሪ የስዕል መግለጫዎቹን ጸሁፉን ከገኘንበት የፌስ ቡክ አምድ ላይ ሊንኩን በመሻን ይመልከቱ Ethiopian Proverbs & Idioms 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *