ሰሞኑን በኦሮሚያ ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ወንዞች ሞልተው ባስከተሉት ጎርፍ በርካቶች ከመኖርያ ከቄዬአቸው ተፈናቅለዋል፤ በንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል። በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጄሬ ወረዳ ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ዳዋ ኢሉ ወረዳ ፣ ምስራቅ ሸዋ ዞን ሊበን ወረዳ፣ አዳማ ፣ ከፊል ፈንታሌ ወረዳ፣ እንዲሁም የመተሃራ እና የመርቲ ከተሞች ፣በአፋር ክልል የአፋምቦ፣ ድብቲ እና አሳኢታ ከተሞች እና አካባቢያቸው በጎርፍ መጥለቅለቅ የደረሰባቸው አካባቢዎች ናቸው።
በአማራ ክልልም ለተከታታይ ሳምንታት በጣለ ዝናብ እንሳሮ እና አንኮበር በተባሉ አካባቢዎች አምስት ሰዎች በጎርፍ ተወስደው ሕይወታቸው አልፏል።በሰሜን ሸዋ ዞን ከ8,000 ሄክታር በላይ የእርሻ ማሳ ላይ ጉዳት ሲደርስ ከ57,000 የሚልቁ አርሶ አደሮች የጉዳቱ ሰለባዎች ሆነዋል። በተጨማሪም 700 የመኖርያ ቤቶች መውደማቸውን እና ከ4500 በላይ ሰዎች በዚሁ ምክክንያት መፈናቀላቸውን የባህርዳሩ ወኪላችን አለምነው መኮንን ዘግቧል ።
የአዋሽ ወንዝ ሙላት ያስከተለው ጎርፍ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን መርቲ-የጁ ወረዳ የእርሻ ማሳ፤ትምሕርት ቤትና መንገዶች ላይ ጉዳት አድርሷል።በአካባቢው ከ70 ሄክታር በላይ የጥጥ አንዲሁም 30 ሄክታር የሚገመት የብርቱካን እርሻ በውሃ መጥለቅለቁን የላይኛው አዋሽ ተፋሰስ አግሮ ኢንዱስትሪ ለዶቼቬለ ተናግሯል። ኃላፊው አቶ መንክር ግርማ ለአካባቢው በጎርፍ መጥለቅለቅ ከቆቃ ግድብ የሚለቀቀው ውሐ ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።
የአካባቢው ገባር ወንዞችም ለደራሽ ውሐው ምክንያት መሆናቸው ተነግሯል።የመርቲ የጁ አንደኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት በጎርፉ ክፉኛ መጎዳቱንም የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህርት ሰዓዳ ከድር ለዶቼቬለ ተናግረዋል።በአሁኑ ወቅት ከመርቲ የጁ ወደ የትኛውም ስፍራ የሚወስዱ መንገዶች በውሃው መሸፈናቸውንም ነዋሪዎች ተናግረዋል።
DW