እነ አቶ ጃዋር መሐመድ በዛሬው ዕለት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ቀርበው የክስ ማመልከቻ ደርሷቸዋል፡፡ በክሱ መሰረት ከ24ቱ ተከሳሾች አቶ ጃዋር መሐመድ በሽብር ወንጀል መከሰሳቸውን በክሱ ላይ ተመልክቷል፡፡ ኢቢሲ

አቶ ጃዋር የሽብር ወንጀልን ለመፈፀም መሰናዳት በሚል ከቀረበባቸው ክስ በተጨማሪ፣ የብሔር ግጭት ማስነሳት፣ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘትና በቴሌኮም ማጭበርበር የሚሉ ክሶችም ይገኙበታል፡፡

በአቶ በቀለ ገርባ እና ሐምዛ አዳነን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾች ላይ የእርስ በርስ ግጭት በማስነሳትና ህገ ወጥ የጦር መሳያ ይዞ በመገኘት በሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፣8 ተከሳሾች ደግሞ በእርስ በርስ ግጭት ማነሳሳት እና መሳተፍ በሚል ክስ እንደቀረበባቸው የክሱ ማመልከቻ ያሳያል፡፡

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ(ኦ ኤም ኤን) የእርስ በርስ ግጭት ማስነሳትና በድርጅቱ መኪና ውስጥ ሕገ ወጥ የጦር መሳያ ይዞ መገኘት በሚል ክስ ቀርቦበታል፡፡

ተከሳሾቹ የክሱን ማመልከቻን ከተቀበሉ በኋላ በችሎቱ ከመነበቡ በፊት የተከሳሽ ጠበቆች ከደንበኞቻቸው ጋር በመምከር አጭር ቀጠሮ እንዲፈቀድ በመጠየቃቸው ክሱን ለማንበብና እና ተያያዥ ትዕዛዞችን ለመስጠት ችሎቱ ለመስከረም 14፣2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል፡፡

በችሎቱ ያልቀረቡ 3 ተከሳሾችን የፌደራል ፖሊስ ይዞ እንዲያቀርብ እና በሌላ መዝገብ ጉዳያቸው እየታየ ዛሬ ያልቀረቡ ተከሳሾች በቀጠሮው ዕለት እንዲቀርቡ ችሎቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ተወካይ ለሐሙስ በተያዘው ተለዋጭ ቀጠሮ ቀን እንዲቀርቡም ፍርድ ቤቱ አዟል፡፡

ኢቢሲ


የሽብርን ጨምሮ  ተደራራቢ ክሶች ከቀረበባቸው መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድ ለሁለተኛ ጊዜ በሽብር መከሰሳቸው በቀጣዩ ምርጫ እንዳይሳተፉ ለማድረግ ታስቦ መሆኑን ለፍርድ ቤት ተናገሩ።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድ በዛሬው ችሎት “ለሁለተኛ ጊዜ በሽብር በመከሰሴ ኩራት ይሰማኛል” ሲሉ ለፍርድ ቤት ተናግረዋል።

አቶ ጃዋር ከዚህ ቀደም ከአገር ውጭ እያሉ ተመሳሳይ ክስ ቀርቦባቸው የነበረ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ስልጣን ሲመጡ ክሳቸው ከተነሳላቸው ሰዎች መካከል አንዱ እንደነበሩ ይታወሳል።

Related stories   Ethiopia:- End Game?

አቶ ጃዋር ጨምረውም ክሱ የተመሰረተባቸው በአገራዊ ምርጫው እንዳይሳተፉ ለማድረግ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፤ ገዢው ፓርቲ በኦሮሚያ ክልል እሸነፋለሁ ብሎ በመስጋቱ የሽብር ክስ እንዲመሰረትብኝ ተደርጓል ሲሉ በችሎቱ ተናግረዋል።

ክሱ እሳቸውን ብቻ ሳይሆን “አቶ እስክንድር ነጋም በአዲስ አበባ ምርጫው ያሸንፋል ተብሎ ተፈርቶ እንጂ፤ ወንጀል ሰርቶ አይመስለኝም” ሲሉም አቶ ጃዋር ሌሎችም ላይ የቀረበው ክስን ጠይቀዋል።

በተጨማሪም አቶ ልደቱ አያሌውን ጠቅሰው ለእስር የተዳረጉት የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚለው ሃሳባቸው ተሰሚነት እያገኘ ስለነበረ ነው ሲሉ አቶ ጃዋር ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

ክሱ የተመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎች ዛሬ ዝርዝሩ በጽሑፍ የተሰጣቸው ሲሆን ችሎቱ ክሱን ለመስማት ለፊታችን ሐሙስ መስከረም 14/2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በዛሬው ችሎት ተጠርጣሪዎቹ የፍርድ ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት ለሃጫሉ ሁንዴሳና የሃጫሉ ግድያን ተከትሎ የተገደሉትን “በሺህዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ጀግኖችን” በህሊና ጸሎት እንድናስብ በማለት ጥያቄ አቅርበዋል።

በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባለፈው ሳምንት ክስ እንደመሰረተባቸው ከገለጻቸው 23 ሰዎችና ኦኤምኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ መካከል 18ቱ ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፤ በማረሚያ ቤት የሚገኙት አቶ ደጀኔ ጣፋና አቶ መስተዋርድ ጀማል ሳይቀርቡ ቀርተዋል።

በተጨማሪም በውጭ አገራት የሚገኙት አቶ ደጀኔ ጉተማ፣ ብርሀነ መስቀል አበበ፣ ፀጋዬ አራርሳ እና የኦኤምኤን ቴሌቪዥን በሌሉበት ጉዳያቸው መሰማት ጀምሯል።

ዐቃቤ ሕግ ባሳለፈው ቅዳሜ አቶ ጃዋርን ጨምሮ በ24 ግለሰቦች እንዲሁም በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኦኤምኤን) ላይ የሽብር ክስን ጨምሮ በአስር ተደራራቢ ወንጀሎች እንደከሰሳቸው ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ክሱ ከተመሰረተባቸውና በእስር ላይ ከሚገኙት ሰዎች መካከል የተወሰኑት ዛሬም [ሰኞ] በተገኙበት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ቀርቦባቸዋል።

በአስር ላይ የሚገኙትን አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሀምዛ አዳነ፣ የኦሮሚያ ሜዲያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን)፣ ዐቃቤ ሕግ ጨምሮ ግለሰቦቹ እና ድርጅቱ ላይ የቀረበው ክስ ዛሬ በንባብ እንደሚቀርብ ጠቁሞ ነበር።

በዚህም መሠረት ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው በጽሑፍ ከተሰጣቸው መካከል አቶ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ እና ሃምዛ አዳነ ይገኙበታል። የኦፌኮ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ደጀኔ ጣፋ በሌላ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው እየታየ ስለሆነ ሳይቀርቡ ቀርተዋል።

Related stories   የሸገር ገበታ ግንቦት 11 ይካሄዳል

የኦኤምኤን ኃላፊ አቶ ደጀኔ ጉተማ፣ የኢትዮጵያ ቆንስላ ዲፕሎማት የነበሩት ብርሃነመስቀል አበበ (ዶ/ር)፣ ነዋሪነታቸው አውስትራሊያ የሆነው አቶ ፀጋዬ ረጋሳን ጨምሮ በአጠቃላይ 24 ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባሳለፈው ቅዳሜ ማስታወቁ ይታወሳል።

በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ የቀረበባቸው ተቋምና ግለሰቦች “እንደየተሳትፏቸው በ1996 የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 240 በመተላለፍ ብሔርንና ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት በመቀስቀስ፣ አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ እንዲነሳሳ በማድግ” የሚሉ ክሶች የቀረቡባቸው መሆኑን አመልክቷል።

በተጨማሪም ተከሳሾቹ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012፣ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 761/2004 እና የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 በመተላለፍ በፈፀሙት ወንጀልም ክስ መስርቷል።

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መስከረም 6/2013 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የወንጀል ችሎት በመዝገብ ቁጥር 260215፤ በአጠቃላይ አስር ተደራራቢ ክሶች የከፈተባቸውና ዛሬ ሰኞ መስከረም 11/2013 ዓ.ም የክሳቸው ዝርዝር የደረሳቸው ተከሳሾችን ዝርዝር ቢቢሲ አግኝቷል።

1. ጃዋር መሐመድ

2. በቀለ ገርባ

3. ሃምዛ አዳነ

4. ጉቱ ሙሊሳ

5. ደጀኔ ጣፋ

6. አረፋት አቡበከር ከድር

7. አማን ቃሉ ባቲ

8. አለማየሁ ገለታ

9. ደጀኔ ጉተማ

10. መለሰ ዲሪብሳ

11. ሸምሰዲን ጣሃ

12. ቦና ባቢሌ

13. ብርሃነስቀል አበበ (ዶ/ር)

14. ጸጋዬ አራርሳ

15. የሃምሳ አለቃ ያዓለምወርቅ አሰፋ

16. ሳጅን ኦላና ጌቱ ተረፈ

17. የ10 አለቃ ታምራት ሁሴን

18. ሳጅን ኦላና በሽር ሁሴን

19. የሃምሳ አለቃ ሰቦቃ ቃቆ

20. የሃምሳ አለቃ ኬኔ ዱሜቻ

21. የሃምሳ አለቃ ዳዊት አብደታ

22. ቦጋለ ዲሪብሳ

23. ማስታዋርድ ተማም እና

24. ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኦኤምኤን) ናቸው።

ታዋቂው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሠኔ 22/2012 ዓ.ም መገደልን ተከትሎ በአዲስ አበባና በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ160 በላይ ሰዎች መገደላቸው እና ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረትም መውደሙ ይታወሳል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችን ጨምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

Related stories   በኦሮሚያ ጭር ያሉ ከተሞች፣ ቀሪው አራት ቀናቶች፣ የኦህዴድ ዝምታና "ቄሮዎች"

BBC Amharic

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *