የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የ2013 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል ሙሉ ሐይማኖታዊ እሴቱና ሥርዓቱ ሳይጓደል እንደሚከበር አስታወቀች።

የቤተክርስቲያኒቱ የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ዐብይ ኮሚቴ አባል የሆኑት መጋቤ ሰላም ሰለሞን ቶልቻ፤ በአዲስ አበባ በርካታ ምዕመናን ተገኝተው የሚያከብሩበት የመስቀል አደባባይ በግንባታ ላይ መሆኑ የበዓሉን ሐይማኖታዊ እሴቱና ሥርዓቱ እንደማያጓድለው ጠቅሰዋል።

በዓሉን ለማክበር የሚታደሙ ምዕመናን ቁጥር በተወሰነ መልኩ መቀነሳቸውን የገለፁት መጋቤ ሰላም ሰለሞን፤ አካባቢው ግንባታ ላይ መሆኑ እና የግንባታ ቁሳቁስ በስፍራው ላይ መኖር እንዲሁም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለዚህ ምክንያት መሆናቸውን አንስተዋል።

መስከረም 16 በመስቀል አደባባይ በመገኘት በዓሉን የሚታደሙና የሚያከብሩ ሰዎች ቁጥር ከ5000 እንደማይበልጥ የተናገሩት መጋቢ ሰላም ሰለሞን፤ የመግቢያ ባጆች ከ3000 እስከ 5000 እንደሚታተሙ ተናግረዋል።

ቤተክርስትያኒቱ ከፀጥታ አካል ጋር በመተባበር በበዓሉ ላይ ለሚታደሙ የክብር እንግዶች እንዲሁም ምዕመናን፣ መዘምራንና ቀሳውስት ባጆችን እንደምታዘጋጅ አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌልና የሐዋሪያዊ ተልዕኮ መምሪያ ኃላፊ የሆኑት መጋቢ ሰላም ሰለሞን ለቢቢሲ አንደገለፁት፤ የ2013 የመስቀል በዓልን ለማክበር ያሉት ተግዳሮቶች ሦስት ናቸው።

አንዱና ቀዳሚው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ነው ያሉ ሲሆን፤ በዚህም ምክንያት በዓሉን ምዕመናኑ በነቂስ ወጥተው አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው ማክበር እንደማይችሉ ተናግረዋል።

ሁለተኛው የፀጥታ ጉዳይ ነው ያሉት ኃላፊው፤ የመንግስት የፀጥታ አካል በዓሉ ያለ ችግር እንዲከበር ከቤተክርስቲያኒቱ የበዓል አከባበር ኮሚቴ ጋር በጥምረት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

ሦስተኛው የመስቀል አደባባይ በግንባታ ሂደት ላይ መሆኑን በማስታወስ፤ የበዓሉ ታዳሚያን ቁጥር ይቀንሳል እንጂ ሐይማኖታዊ ሥርዓቱ ሳይጓደል ይከበራል ሲሉ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በበዓሉ ላይ የሚቀርቡ ያሬዳዊ ዝማሬዎች፣ በሊቃውንቱ መካከል የተዘጋጁ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን መዝሙሮችና የሙሉ ትርዒቱ ዝግጅት መጠናቀቃቸውንና እንደሚቀርቡም አመልክተዋል።

የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ቅዱስ ፓርቲያሪኩን ጨምሮ ይገኛሉ ያሉት መጋቢ ሰላም ሰለሞን፤ ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላላ ሊቃውንትና ካህናቱ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በሚመለከት ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚሰጠው ምክር ተግባራዊ እንደሚደረግ የሚናገሩት ኃላፊው፤ አካላዊ ርቀት መጠበቅ እንዲሁም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ በበዓሉ አከባበር ወቅት የሚተገበሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

Related stories   በቦረና ዞን በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ8 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ተያዘ

ከዚህ በፊት የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች፣ ከምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤና ከፀጥታ አካል ጋር በመሆን በመስቀል አደባባይ ጉብኝት ማድረጋቸውን የገለፁት ኃላፊው፤ በዚህም ምልከታ እንግዶች በየት በኩል እንደሚስተናገዱ፣ መዘምራን በየት በኩል ዝማሬ እንደሚያቀርቡ እንዲሁም ደመራ እንዴት እንደሚደመር ጥናት መደረጉን ገለፀዋል።

በርካታ ቱሪስቶችና የውጭ አገራት ዜጎች ይታደሙበት የነበረው የመስቀል ደመራ በዓል በኮሮናቫይረስ ምክንያት የቱሪስቶች እንቅስቃሴ በዓለም ዙሪያ በመስተጓጎሉ በዚህ ዓመት እንደከዚህ ቀደሙ ብዙ ጎብኚዎች ላይገኑ ይችላሉ።

የመስቀል ደመራ በዓል በኢትዮጵያ በርካታ ሕዝብ ታድሞባቸው ከሚከናወኑ ሐይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርትና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት እንደተመዘገበም ይታወቃል።


ሙሉ ዘገባው የቢቢሲ አማርኛ ነው


 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *