ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ አቶ ጃዋር መዝገብ የተመሰረተውን ክስ ለማንበብ ለመስከረም 21/2013 ቀጠሮ ያዘ።

By BBC Amharic

በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ የተመሰረተውን ክስ ለማንበብ ቀጠሮ ይዞ የነበረ ቢሆንም ከተከሳሽ ጠበቆች በቀረበ ጥያቄ መሰረት ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ተደርጓል።

በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ ከዚህ በኋላ እነ አቶ ጃዋርን ጨምሮ ሌሎች 18 ተከሳሾች ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ አዟል።

እስካሁን ድረስ እነ አቶ ጃዋር አዲስ አበባ ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል ይገኙ ነበር።

የዛሬ ውሎ

በዛሬው ችሎት በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ ስር ከተከሰሱትና በአገር ውስጥ ከሚገኙት መካከል አቶ ደጀኔ ጣፋ እና አቶ መስተዋርድ ተማም ለሁለተኛ ጊዜ አልቀረቡም።

ከአገር ውጪ የሚገኙ ተከሳሾችን በተመለከተም ፖሊስ እነዚህ ተከሳሾች ለማቅረብ የተሰጠው ጊዜ ቀጠሮ አጭር ስለሆነ ለማስፈፀም እንዳልቻለ ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

ጠበቆች በበኩላቸው እነዚህ ሰዎች ውጪ አገር እንዳሉ እንዲሁም ክሱ በሌሉበት እንደተከፈተ እየታወቀ፣ ፖሊስ ይዞ እንዲያቀርብ በሚል ምክንያት ቀጠሮ ማስረዘም ትክክል አይደለም በማለት ተከራክረዋል።

Related stories   ሰበር ዜና - ቀዳማዊት እመቤት 12ኛውን ትምህርት ቤት አስረከቡ

የአቶ ደጀኔ ጣፋንና መስተዋርድ ተማምን ጉዳይ በተመለከተ ሁለቱ ተከሳሾች በሌላ መዝገብ ተከሰው ስላሉ በዛሬው ቀጠሮ ላይ መቅረብ እንዳልቻሉ ዐቃቤ ሕግ አስረድቷል።

በሌላ በኩል አቶ ደጀኔ ጣፋ በቤተሰቦቻቸው እየተጎበኙ እንዳልሆነ እና አስፈላጊውን ነገሮች እያገኙ እንዳልሆነ ጠበቃቸው ለፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን አሰምተዋል።

በዛሬው ችሎት ላይ የተናገሩት አቶ ሸምሰዲን ጠሃ ታመው ሐኪም ቤት እየተመላለሱ እንዳሉ በመግለጽ የሕክምና ቀጠሮ እያለባቸው በመከልከላቸው ሕመማቸው እየበረታባቸው መሆኑን በማንሳት አቤቱታ አቅርበዋል።

ክስ ለመስማት ለዛሬ ተይዞ የነበረው የችሎት ቀጠሮ በአቶ ደጀኔ እና አቶ መስተዋርድ አለመገኘት የተነሳ ክሱ ይነበብ አይነበብ በሚለው ላይ በጠበቆች እና በዐቃቤ ሕግ መካከል ረዥም ክርክር ተካሂዷል።

ጠበቆች፤ ደጀኔ እና መስተዋርድ ስላልቀረቡ ክሳቸው በአንድ ቦታ መሰማት አለበት፣ እኛም ያለንን ተቃውሞ በአንድ ቦታ ስለምናቀርብ ሌላ ቀጠሮ ይሰጠን ሲሉ ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል ሌሎች በዚህ መዝገብ ስር የተከሰሱ ተከሳሾችን በሚገኙበት ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ አግኝተን ለማወያየት አልቻልንም በማለት ጠበቆች ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

ወደ ማረሚያ ቤት

ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾችን ክሱ እጃቸው ከደረሰ በኋላ አሁን በጊዜያዊነት ከቆዩበት ስፍራ ወደ ማረሚያ ቤት በመሄድ ተመሳሳይ ወደ በሆነ ቦታ መታሰር አለባቸው ሲል ጠይቋል።

Related stories   የትግራይ ረሃብ ድሮም ተደብቆ የኖረ ወይስ አዲስ በሁለት ወር የተፈጠረ? ገለልተኛ ፈራጅ ያጣው አወዛጋቢው አጀንዳ! – ሪፖርት

ጠበቆች በበኩላቸው ከአንድ እስከ ሦስት ያሉት ተከሳሾች በፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያላቸው ስለሆኑ ለደኅንነታቸው ሲባል አሁን እንዲቆዩ ከተደረገበት ስፍራ መቀየር የለባቸውም ሲል ተከራክሯል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

በዚህም መሰረት ተከሳሾች የሚቆዩበትን በተመለከተ ተከሳሾች ከአሁን በኋላ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ ትዕዛዝ አስተላልፏል፟።

ከሳምንት በፊት ፍርድ ቤቱ በሽብር ድርጊት ክስ የቀረበባቸው የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋን ጉዳያቸውን ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በመሆን አንዲከታተሉ መወሰኑ ይታወሳል።

ውጪ አገር ያሉ ተከሳሾችን በተመለከተ የፌደራል ፖሊስ በሚቀጥለው ቀጠሮ ላይ ቀርቦ የደረሰበትን እንዲያብራራ አዟል።

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *