በአዲስ አበባ የ13ኛ ዙር የጋራ መኖሪያ ቤቶች እድለኞች እና የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ዛሬ ካርታ፣ ቁልፍ እና ውል ርክክብ በይፋ ተጀመረ።

በከተማ አስተዳደሩ እየተከናወነ ባለው መርሃ ግብር 51 ሺህ 229 የጋራ መኖሪያ ቤት እድለኞች እና 22 ሺህ 915 የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ካርታ፣ ቁልፍ እና ውል መረከብ ጀምረዋል።

የካርታ፣ ቁልፍና ውል ርክክቡ ዛሬ በይፋ የተጀመረ ሲሆን፥ የሁሉም የጋራ መኖሪያ ቤት እድለኞች እና የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች እስከ ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓመተ ምህረት ድረስ ይረከባሉ ተብሏል።

በዛሬው እለትም ከእደለኞቹ እና የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የተመረጡ 100 ግለሰቦች ከአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እጅ ቁልፍ፣ ካርታና ውል ተረክበዋል።

ቀሪዎቹ የቤት እድለኞች እና የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች በየክፍለ ከተሞቻቸው ርክክብ መፈፀም እንደሚችሉ ተጠቁሟል።

የከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ በተለያዩ መርሃ ግብሮች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እየገነባ በእጣ ሲያስተላልፍ ቆይቷል።

ለዓመታት በአዲስ አበባ እየተከናወነ በነበረው የልማት ስራ ከቀያቸው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ለተለያዩ ምጣኔ ሃብታዊ ችግር መጋለጣቸውን ተከትሎ የከተማዋ አስተዳደር መዲናይቱ በዙሪያዋ የሚገኙ አርሶ አደሮችን የምትገፋ ሳይሆን አብራቸው የምታድግ እንድትሆን የልማት ተፈናቃይ አርሶ አደሮችም የዚህ የቤት ልማት መርሃ ግብር ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ተግባር መጀመሩ ይታወሳል።

በዳዊት መስፍን

Related stories   በደቡብ ክልል በተከሰተው ግጭት የተጠረጠሩ 1 ሺህ 130 ሰዎች ተይዘው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *