ቢቢሲ – በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ረቡዕ መስከረም 27/2013 ዓ.ም በርካታ ሰዎች በከተገደሉበት ጥቃት ጋር በተያያዘ 30 የሚሆኑ ‘ሽፍታዎች’ መገደላቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ለቢቢሲ ገለጹ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አብዱልአዚም መሐመድ እንደገለጹት ሰሞኑን በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት አንድ ቻይናዊን ጨምሮ 13 ሰዎች በታጣቂዎቹ ተገድለዋል።

ይህንን ተከትሎ የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ጥቃቱን ፈጽመዋል የተባሉ 30 የሚሆኑ የክልሉ ፖሊስ ሽፍታዎች ያላቸው ላይ እርምጃ ተወስዶባቸው ሲገደሉ ሦስቱ ደግሞ መማረካቸውን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ከባለፈው ዓመት ማብቂያ አንስቶ ማንነታቸው በይፋ ያልተገጹ ታጣቂዎች በክልሉ ውስጥ ባሉ ወረዳዎች በፈጸሟቸው ጥቃቶች ሳቢያ በርካታ ሰዎች መገደላቸውና ንብረት መውደሙ ይታወሳል።

ባለፈው ረቡዕ በተፈጸመው ጥቃትም ታጣቂዎቹ ግድያውን የፈጸሙት ግለሰቦቹ ሲጓዙባቸው የነበሩ ተሽከርካሪዎች አስቁመው እንደሆነ ኮሚሽነር አብዱልአዚም መሐመድ ገልጸዋል።

ኮሚሽነሩ ጨምረው እንዳብራሩት ጥቃቱ የተፈጸመባቸው መንገደኞች በአካባቢው ካለው የጸጥታ ሁኔታ አንጻር መከላከያ ሠራዊትና የፀጥታ ኃይሎች የመንገዱን ደኅንነት እስኪያረጋግጥ ድረስ ባሉበት እንዲቆዩ ተጠይቀው እንደነበር ተናግረዋል።

ነገር ግን ቻይናዊው መንገደኛ የነበረበት ተሽከርካሪ የተሰጠውን የጥንቃቄ መመሪያ ችላ ብሎ ጉዞውን መቀጠሉን ተከትሎ ሌላ አውቶብስ በተመሳሳይ ሁኔታ መንገዱን መቀጠሉን አመልክተው፤ በእነዚህ በሁለት ተሽከርካሪዎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት ሰዎች መገደላቸውን አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም የተከሰቱ ጥቃቶችን በተመለከተ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ጸረ ሰላም ኃይሎች መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ጥቃት አድራሾቹ በአገር ውስጥና በውጭ ኃይሎች የሚደገፉ መሆናቸውንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

Related stories   ኦፌኮ ራሱን ከምርጫው ማግለሉን አረጋግጧል

የአካባቢውን ፀጥታ ለመጠበቅ ሕዝቡ ከፀጥታ ኃይል ጎን ሆኖ ሽፍቶቹን እየተዋጋ መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፤ በአካባቢው ሕብረተሰቡን የማጠናከር ሥራ እንዲሁም የፀጥታ ኃይሎችም በተጠናከረ ሁኔታ ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም በክልሉ ከጳጉሜ 2 ጀምሮ ለሳምንት በዘለቀ ጥቃት፤ ማንነታቸው ያልታወቀ የታጠቁ ኃይሎች በተለያዩ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢዎች በፈጸሟቸው ጥቃቶች ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች መገደላቸውና ንብረት ላይም ጉዳት መድረሱን ይታወሳል።

በወቅቱ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በጥቃቱ እስከ 50 የሚደርሱ ሰዎች መሞታቸው ሲገልጹ፤ የወደመውና የተዘረፈውን ንብረት መጠን ግን ማወቅ እንዳልቻሉ ተናግረው ነበር።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም ባወጣው መግለጫ በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ የፀጥታ መደፍረሶችን ተከትሎ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከተፈጸሙ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ እጅግ አሳሳቢ መረጃዎች እየደረሱት መሆኑን ባወጣው መግለጫ አመልክቶ ነበር።

በወቅቱ እነዚህ መረጃዎች እየደረሱት ያለው በክልሉ ውስጥ ከሚገኘው መተከል ዞን፣ ከቡለን ወረዳ አጳር ቀበሌ እንዲሁም ከወንበራ ወረዳ መልካን ቀበሌ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።

በክልሉ ጳጉሜ 1/2012 ዓ.ም እንዲሁም ከመስከረም 4 እስከ መስከረም 10/2013 ዓ.ም መካከል ባሉት ቀናት ውስጥ ቢያንስ ሁለት ጥቃቶች ማጋጠማቸውን ከክልሉ መንግሥት ለማረጋገጥ መቻሉንም በዚያው መግለጫ ላይ አመልክቷል።

Related stories   ኦፌኮ ራሱን ከምርጫው ማግለሉን አረጋግጧል

ቢያንስ በሁለት ዙር በተፈጸሙት ጥቃቶች ባልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያዎች መፈፀማቸውን እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን በስፍራው ከሚገኝ አንድ መንግሥታዊ ምንጭ መረዳት እንደቻለ ኮሚሽኑ መግለፁ ይታወሳል።

በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር በመከላከያ ሠራዊት፣ በፌዴራል ፖሊስ እና በክልል የጸጥታ ኃይሎች ሰላምን ለማስጠበቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያበረታታም አስታውቋል።

ኮሚሽኑ አገሪቱ በተቀበለቻቸው ሕጎችና ሰነዶች መሰረት የሰዎች በሕይወት የመኖር መብቶች እንዲከበሩ የጠየቀ ሲሆን፣ በክልሉ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ማጋጠማቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ገለልተኛ፣ ፈጣን ምርመራዎችን በማካሄድ ግድያው በተከሰተባቸው ሁኔታዎች ላይ የጥፋተኞችን ተጠያቂነት እንዲያረጋግጡ አሳስቦ ነበር።

በተጨማሪም የክልሉ መንግሥት አካላት ተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸው ወደ ቀደመ ሕይወታቸው የሚመለሱበትን መንገድ እንዲያመቻቹ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።

ከዚያም በኋላ በክልሉ ማንዱራ ወረዳ በንገዝ በተባለ ቀበሌ ውስጥ ሐሙስ መስከረም 14/2013 ሌሊት ላይ በተፈፀመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ በድጋሚ በተፈፀመ ጥቃት ቢያንስ የ15 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገልጾ፤ ሁኔታው አሳሳቢነቱ በእጅጉ እንደጨመረ ማመልከቱ ይታወሳል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተደጋጋሚ ያጋጠሙ ጥቃቶችን ተከትሎ ክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በኮማንድ ፖስት ስር እንዲተዳደሩ የተወሰነ ሲሆን የመከላከያ ሠራዊትና የፌደራል ፖሊስ በአካባቢዎቹ ሰላም እንዲያስከብሩ ተሰማርተዋል።

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *