ከአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ ክስ የቀረበባቸው ተከሳሾች የክስ መቃወሚያ የሌላቸው መሆኑን ለፍርድ ቤት ገልፀዋል
 
በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ዙርያ ክስ የቀረበባቸው 1ኛ ጥላሁን ያሚ፣ 2ኛ ከበደ ገመቹ፣ 3ኛ አብዲ አለማየሁ፣ እና 4ኛ ላምሮት ከማል፤ ዛሬ ጥቅምት 04/2013 ዓ.ም ለነበራቸው ቀጠሮ ያላቸውን የክስ መቃወሚያ ይዘው እንዲቀርቡ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ቀርበው ቀድሞ በነበራቸው ቀጠሮ ላይ ሶስቱ ተከሳሾች አቅም ስለሌለን መንግስት ጠበቃ ያቁምልን በማለት ጠይቀው የነበረ ሲሆን፤ 4ኛ ተከሳሽ ደግሞ ጠበቃ በግሌ የመቅጠር አቅሙ ቢኖረኝም ፍቃደኛ ሆኖ ጥብቅና የሚቆምልኝ ሰው ማግኘት ባለመቻሌ ጠበቃ ይመደብልኝ በማለት ጠይቀው የነበረ በመሆኑ በመንግስት ጠበቃ ተመድቦላቸው ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡
የተከሳሾቹ ጠበቃ በበኩላቸው፤ 4ኛ ተከሳሽ ላምሮት ከማል ጠበቃ በግል የመቅጠር አቅም እያላቸው ከህግም አንፃር ተገቢ ባለመሆኑ መንግስት በነፃ ጠበቃ ሊያቆምላቸው አይገባም በሚል ቅሬታቸውን አቅርበው፤ ፍርድ ቤቱም በበኩሉ ትዕዛዙ የተሰጠው ህጎችን ከግንዛቤ በማስገባት በመሆኑ ፍትህ እንዳይጓደል ትዕዛዙ በነበረው መሰረት እንዲቆይ በማለት ለጠበቃው ምላሽ በመስጠት ችሎቱ እንዲቀጥል አድርጓል፡፡
ችሎቱ ቀጥሎም ተከሳሾቹ ዛሬ በነበራቸው ቀጠሮ መሰረት በተመደበላቸው ጠበቃ አማካኝነት በቀረበባቸው ክስ ላይ ምንም የክስ መቃወሚያ የሌላቸው መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል፡፡
በመቀጠልም የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው እያንዳንዳቸው ተከሳሾች በክሳቸው ላይ የተጠቀሰውን ወንጀል አልፈፀምኩም በማለት ቃላቸውን ለፍርድ ቤቱ ሰጥተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም የተከሳሾችን ምላሽ ካዳመጠ በኋላ የዐቃቤ ህግን ምስክሮች ቃል ለመስማት ለህዳር 23, 24 እና 25 ቀጠሮ በመስጠት የእለቱ ችሎት ተጠናቋል፡፡
ምንጭ ጠቅላይ አቃቤ ህግ 
Related stories   የኢህአዴግ "ቀኝ እጅ" HR 128/SR 168 የተሰኘውን ህግ እንደ HR2003ቱ ህግ ሊያመክኑት?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *