ተመስገን መረጃ ከሌለው በፕሬስ ህጉ መሰረት ይቅርታ ጠይቆ ማስተባበያ ማተም አለበት፤ መርጃም ካለው ይህንኑ ግልጽ ማድረግ ይገባዋል። ከዛ ህዝብ ይፈርዳል። በተድበሰበሰ ጉዳይ ህዝብ ሁለት ጎራ ይዞ የሚቧቀስበት ምክንያት ሊኖር አይገባም፤

ተመስገን ደሳለኝ በማኔጂንግ ዳይሬክተርነት በሚመራው የፍትህ መጽሄት ” ፍትህ አጓድሏል” በሚል መታሰሩ ከተሰማ ጀምሮ በርካታ አስተያየቶች እየተደመጡ ነው። ክርክር ያስነሳው ጉዳይ ደሳለኝ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ስም ጠቅሶ የጻፈውና ህዝብ ዘንድ የደረሰው መረጃ ነው። ሲፈታ “የሐሰት ወሬ በማሰራጨት ትፈለጋለህ ከሚል ውጪ የነገሩኝ ነገር የለም” ብሏል። ተመስገን መፈታቱን ወንድሙ ነው ያረጋገጠው።

ይህንን ተከትሎ ያለማስረጃ ስም ማጥፋት ሊፈቀድ እንደማይገባ ለጠቀሱ የፊስ ቡክ ተጠቃሚ ስድብ ሲመለስላቸው፣ ” ተመስገን ሃሳቡን ጻፈ፣ እኔስ ለምን ሃሳቤን ስጽፍ እሰደባለሁ?” ሲል ሙግት ገጥመው ታይተዋል። በዚሁ ሙግት ስር የጎላው ሃሳብ “ተመስገን መረጃ አለው ወይ?” የሚለውና እሳቸው የተኳቸው የቀድሞው ጠቅላይ አቃቤ ህግ ” አፋጠጧቸው” የሚለው የፍትህ መጽሄት መረጃ ነው። አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ በፍጥነት ከሃላፊነታቸው የተነሱበትን ምክንያቶችም የዘረዘሩ በርካታ ናቸው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሰፊ መከራከሪያ የሆነውና የህግ ባለሙያ ማብራሪያ የሰጡበት የተመስገን እስርና ከሳሽ ጉዳይ ጠማማነት ነው። የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ምን አግብቶት ከሳሽ ይሆናል? ተመስገንስ መረጃ ከሌለው ህጉ የሚያዘውን ለምን አያደርግም?

ተመስገን ያተመው ጽሁፍ ላይ ” እሷ” እያለ ያነሳው ጉዳይ ሲጨመቅ “በአንድ  የODP ስብሰባ ላይ 40 ሚሊዬን ብር በባንክ ሂሳባቸዉ መገኘቱ ተነስቶላቸዉ ገንዘቡ ያለእሳቸዉ እዉቅና በሂሳባቸዉ መግባቱን አምነዋል” የሚል ነው። ይህንኑ ጉዳይ አንስቶ ሲያፋጥጡ የነበሩት ደግሞ ” አንተ እሱ” ተብለው የተጠቀሱትና በአጭር ጊዜ ተገምግመው በወይዘሮ አዳነች የተተኩት የቀድሞው አቃቤ ህግ አቶ ብረሃኑ ጸጋዬ ናቸው። የፍርድ ሂደቱ የሚቀጥል ከሆነ አንዱ አስረጂ ምስክር እሳቸው እንደሚሆኑ ነው።

ተመስገን መታሰሩ ይፋ ከመሆኑ በፊት የኦሮምያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ኃልፊ አቶ ታዬ ደንደአ በፌስ ቡክ ገጻቸው ” የODP ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በሙሉ የዚህን ወሬ ሀሰተኝነት ሊያረጋግጥ ይችላል። በቅርቡ በተካሄደዉ ኮንፈረስ ላይ እነማን በሌብነት ተገምግመው ፋይላቸዉ እየተጣራ እንደሆነም የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራር በትክክል ያዉቃል። ሸገር ላይ በሌብነት የደለበዉ ስግብግብ ቀድሞ ለማጥቃት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የጀመረ ይመስላል።” ሲሉ አትመዋል። ዝርዝር ጉዳዮችንም አንስተዋል።

Related stories   አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ቀጠሮ ተሰጠባቸው

በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ካቢኔ ጽህፈት ቤት ለብሮድካስት ባለስልጣን ” የፍትህ መጽሄት ያወጣውን ሃሰተኛ መረጃ ይመለከታል” ሲል በጻፈው ደብዳቤ ” … የፍትህ መጽሄት አዘጋጅ ሆን ብሎ የአመራር ስም በማጥፋት ሃሰተኛ መረጃ ለሕዝብ በማድረስ ሕዝብን በመንግስት አካል ላይ የማነሳሳት ድርጊት በመፈጸሙ ሊጠየቅልን ይገባል ብለን እናምናለን” ካለ በሁውላ አክሎ ” … ተቋማችሁ የፍትህ መጽሄት ይህን መረጃ ከየት አግኝቶ እንደተጠቀመው ማብራሪያ እንዲሰጠንና በሕግ አግባብ እንዲጠየቅ እንድታደርጉልን እንጠይቃለን” በማለት ያጠይቃል።

ለህግ ቅርብ የሆኑ ወገኖችን ዝምታ የሰበረው ይህ ደብዳቤ በመሆኑ ዛጎል ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የህግ ባለሙያን ምክር ጠይቋል። የህግ ባለሙያው እንዳሉት ” ተመስገንን ለመክሰስ ብልፅግና ፓርቲም ሆነ ፣ ማዘጋጃ ቤት አያገባቸውም” አያይዘውም  ” እንዲህ ብሎ ነገር የለም። በፕሬስ ሕጉ አቃቤ ህግ ወይም ራሳቸው ወይዘሮ አዳነች ናቸው መክሰስ የሚችሉት። በትክክለኛው አሰራር ግን ተመስገን ይቅርታ ከጠየቀና ካስተባበለ ጉዳዩ ይሞታል” ብለዋል።

“በዚህ ጉዳይ ተመስገን ማስረጃ ይኖረው ይሆን?” ሲሉ ጠይቀው መረጃ ካለ በሁሉም ወገን ብዙ ግርግር አያስፈልግም በፍርድ ሂደቱ ላይ ይፋ ይሆናል። ተመስገን ግን ክሱን ከእስር ነጻ ሆኖ ሊከታተል ይገባዋል” ያሉት የህግ ባለምያው፣ የባንክ ስቴትመንት ተብሎ የወጣው መረጃ ብዙም እንዳልጣማቸው ገልጸዋል። “መረጃው የወይዘሮዋ የአራት ወር ደመወዝ የሚያሳይ ነው። ይሄ ብቻ ነው አካውንታቸው ማለት ይከብዳል። የተመስገንም ድፍረት ትክክል አይደለም። ብዙ መንገድ ተጉዞ ማጣራት ይገባው ነበር። ይህን ሳያደርግ ቀርቶ ያለ ማስረጃ ከሰራ ግን ከተጠያቂነት ሊያመልጥ አይችልም። ማምለጫው በፕሬስ ህጉ መሰረት ይቅርታ ጠይቆ ፋይሉን መዝጋት ብቻ ነው ” የሚል ሃሳብ ሰጥተዋል። ከምንም በላይ ግን ተመስገን መረጃ ከሌለው ይቅርታ ጠይቆ ጉዳዩ ቢዘጋ፣ መረጃ ከሌለውም ራሳቸው ወይዘሮ አዳነች ወይም የግል ጠበቃ ቀጥረው፣ ተመስገንም ነጻ ሆኖ ተሟግቶ ፍትህ ሲሰጥ ቢያዩ ደስታቸው መሆኑንን ገልጸዋል።

ተመስገን ታስሮ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንደገባ የገለጸው ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ነበር።ተመስገን ከቢሮ መወሰዱን እንደሰማ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አምርቶ በር ላይ ያሉት ፖሊሶች ተመስገንና የመፅሔቱ አዘጋጅ ምስጋን ዝናቤ ተይዘው መግባታቸውን እንዳረጋገጡለት ጠቁሟል።

 ተመስገን በፖሊስ ለምን እንደታሰረ እስካሁን የትኛውም መንግስታዊ ተቋም ያለው ነገር የለም።
ይሁንና ተመስገን ባሳላፍነው ቅዳሜ በፍትህ መጽሄት ከብር ቅያሬው ጋር ተያይዞ ባወጣው የትንታኔ ዘገባ ምክንያት ለእስር ሳይዳረግ እንዳልቀረ በርካቶች ግምታቸውን በመስጠት ላይ ናቸው። ተመስገን ለረጅም አመታት በእስር ቤት ቆይቶ የእስር ጊዜውን ጨርሶ ከተፈታ ገና ሁለት አመቱ ነበር።
በመጨረሻ በተሰራጨ መረጃ ተመስገንና  የመፅሄቱ አዘጋጁ ምስጋናው ዝናቤም ተለቀዋል። ቢቢሲ ያነጋገረው ወንድሙ ነው። ለምን በቁጥጥር ስር እንደዋለም ይሁን የተፈታተበትንም ምክንያት በተመለከተ ምንም አይነት መረጃ እስካሁን እንዳላገኙም ታሪኩ አስረድታቷል። በትናንትናው ዕለትም ታሪኩ ለጥቂት ደቂቃዎች እንዳገኘውና ለምን እንደታሰረ በጠየቀው ወቅት “የሐሰት ወሬ በማሰራጨት ትፈለጋለህ ከሚል ውጪ የነገሩኝ ነገር የለም።” ሲል ተናግሯል።

 

Related stories   የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ የታቀደ መሆኑን የሚያመላክቱ ማስረጃዎች ተገኝተዋል- ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *