የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አክሱምን፣ አድዋንና የአዲግራትን ዙሪያ መቆጣጠሩን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ማጣሪያ አስታወቀ። የጠራ መረጃ እንዲያቀርብ የተቋቋመው ማዕከሉ ይህንን የድል ዜና ይፋ ከማድረጉ ሰዓታት በፊት ድምጸ ወያኔ የተሰኘው የትህነግ ልሳን የአገር መከላከያ ሰራዊት ራያንና ሽሬን ለቆ በመፈርጠጥ ላይ መሆኑንን ሲአስታውቅ። የአየር ሃይል ዋና አዛዥ የትህነግን ወሬ የተስፋ መቁረጥ ኑዛዜ መሆኑንን ጠቁመው ” በልዩ ኦፕሬሽን ዋናዎችሁን እንይዛቸዋለን” በማለት አየር ሃይል ዶግ አመድ እንደሚያድርጋቸው በራስ መተማመን ስሜት አስታወቀው ነበር።
መግለጫው እንዳለው በምዕራብ ግንባር የሕወሓት ጁንታን ኃይል እያጠቃ ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ ከሽሬ በኋላ ሰለህለሃ ላይ የመሸገ የሕወሓት ኃይል ገጥሞት ውጊያ ገጥሞ እንደነበር አመልክቷል። ይሁን እንጂ ሰለህለሃ ላይ የመሸገው የጁንታው ኃይል መንገዱን በዶዘር ቆርጦና አስፓልቱን አበላሽቶ በቦታው ከባድ መከላከል ቢያደርግም የመከላከያ ሰራዊት የጁንታውን ተከላካይ ኃይል ሰብሮ በመግባት አክሱምን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩ በእጁ አስገብቷል።
ከአክሱም ወደ አድዋ በነበረው ጉዞ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የጁንታው ኃይል ለመከላከል ቢሞክርም፣ የአገር አደራ የተቀበለው የአገር መከላከያ ሰራዊት ድል እንደተቀዳጀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ማጣሪያ ገልጿል። ማጥቃቱን የቀጠለው የአገር መከላከያ ሰራዊት እንቲጮንና የአዲግራትን ዙሪያ ተቆጣጥሮ ወደ አዲግራት ከተማ እየተምዘገዘገ ነው።
የአገር መከላከያን ምት መቋቋም ያልቻለው ቁጥሩ የበዛ የጁንታው ተዋጊዎች እጃቸውን የሰጡ ሲሆን ከድተው ከጁንታው ጋር ሆነው ሲዋጉ የነበሩ ወታደሮችም ዳግም መከላከያ እጅ መውደቃቸው ተገልጿል።
በሽንፈት አረንቋ ውስጥ ወድቆ እያዳከረ ያለው ይትህነግ ጁንታ ሃይል እርቅ እያለ እየለፍለፈ፣ በሌላ በኩል ሮኬት እየወረወረ ነው። ይህን ትንኮሳ ተከትሎ የአየር ሃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የአጻፋ እርምጃ እንደሚወሰድና የጁንታ ሃይል ያሉትን ህዝብ ሳይጎዳ በልዩ ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር እንደሚውል አስታወቀው ሃያ አራት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው የድል ዜናውን መንግስት ይፋ ያደረገው።
አኩም ቤተ ክርስቲያንና አካባቢው ላይ መሽጎ የነበረው ሃይል ሲመታ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ አንዳችም ጉዳት እንዳልደረሰ ታውቋል። መንግስት እንዳስታወቀው ጁንታው ባለቀ ሰዓት ሰላማዊ ዜጎችን በመድፍ እየደበደበ ነው።