በትግራይ ይደረጋል የተባለውን ያመነ አልነበረም። የህግ ማስከበሩ ዘመቻ ሲጀመር ስላቅ ነበር። ” እናደቃችኋለን፣ ትግራይ መሬትን የረገጠ ከቶውንም አይወጣም” የሚል ዘፈን እንጂ ዘመቻው በዚህ መልኩ ያልቃል ብሎ የገመቱት አድራጊዎቹ ብቻ ነበሩ። ከዘመቻው መጠናቀቅ በሁዋላ መቀሌ በመገኘት ከትናት በስቲያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ያረጋገጡት ሃቅ ቢኖር ይህ ነበር። ሁሉም ሆኖ ግን አንድ ጥያቄ አለ። ትግራይ ከዛስ? ልጆቿስ ምን አስበዋል? ሰማኒያ ሺህ ሰራዊት የት ገባ?
ዛሬ ከትግራይ የሚወጡት ዜናዎች መብራት ተመለሰ፣ ስልክ በከፊል ሰራ፣ አገልግሎት ጀመረ፣ የሚሉና ከሁሉም በላይ አዲሱ ጊዚያዊ አስተዳደር ስራ መጀመሩን የሚያመላክቱ ሆነዋል። የትህነግ ከፍተኛና አመራሮች  አንጋፋ ፊት አውራሪዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ” ነበር” ቢቀየሩም አስካሁን ” ትግራይ ከዛስ?” የሚለው ጥያቄ በብዙ መልኩ ከየአቅጣጫው ሲሰነዘር ይሰማል።
PM Abiy to Tigray: 'You Are the Motor that Runs Ethiopia'
ሰማኒያሺህ የትህነግ ታጣቂ ሃይል የት ገባ?
ይህ ሪፖርት ከመዘጋጀቱ በፊት ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑና መቀሌ ስራ ላይ የነበሩ እማኞችን ለማነጋገር ተሞክሯል። ቀደም ሲል የነበሩ ሁነቶችም እንደ ግብአት ለማነጻጸሪያ ተወስደዋል። ለመነሻ ዋና ጉዳይ እንዲያመች ኢራቅን ትንሽ እንያት።
አሜሪካ ለኩዌት ተቆርቋሪ ሆና ኢራቅን በበርሃው ማዕበል ጦሯ አማካይነት ያርበደበድችው ገና ፍልሚያው እንደተጀመረ ነበር። ከፍልሚያው በፊት አሜሪካኖችን ” እቀነጥሳቸዋለሁ፤ በረሃ ውስጥ አስቀራቸዋለሁ” እያለ የቆጥ የባጡን ሲፎክርና ሲአይስፎክር የነበረው ሳዳም ሁሴን የመጨረሻ እጣው መንጠልጠል ነበር።
ያ ሁሉ መፈክር ቀልድ እንደ ጉም ተኖ ለዲስኩርና ለቲያትር መዝናና ከመዋሉ በቀር ለሳድምም ሆነ ሳዳም ላደራጀው ሃይል የፈየደው ነገር አልነበረም። ሳዳምን ጉድጓድ ውስጥ ይዘውት ሲሳለቁበት አየን። በመጨረሻም በሚያሳዝን መልኩ ሰቀሉት። አዎ ደርጊቱ ክብረ ነክ ቢሆንም ከመሆን ሊከለክል የሚችል ሃይል አልነበረም። ከዛስ ምን ሆነ?
የኢራቅ ገዢው ትልቁ የባዝ ፓርቲ ሙሉ በሙሉ እንዲበተን ተደረገ። ፓርቲው ብቻ አይደለም ሰራዊቱ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተገፋ። ይህን ጊዜ የጦር መኮንኖች ተሰባስበው የአማኤሪካን መንግስትን ወኪሎች፣ የዘመቻው መሪዎችን የጦር መኮንኖችን፣ አግባብ ያላቸውን ዲፕሎማቶችን በተደጋጋሚ የባዝ ፓርቲን መበተን ችግር ያመጣል። ሰፊ ቁጥር ያለውን ጦር ሲመራ የነበረ ፓርቲ መበተን ሰራዊቱና መሪዎቹን ወደ ሌላ ሃሳብ ይመራቸዋል ቢባል አሜሪካኖቹ በበረሃው ማዕበል ድል ሰክረው ነበርና ከሳዳም ስቅላት በሁዋላ ያሳሰባቸው ነገር ስላልነበር ጥያቄውን ውድቅ አደረጉት። እናም ሁሉም ላይመለሱ ተበተኑ።
ጦርነቱን ሸሽቶ ወደ ቤቱ የገባ፣ በሳዳም ተማሮ መዋጋት ያልፈለገው ሁሉም በጅምላ ደሞዝ ሲቆምበትና ሲቸገር እያደፈጠ ይተኩስ ጀመር። እየተደራጀ ያጠቃ ገባ። እየመሸገ ያነድ ጀመር። በአካባቢነትና በዘር እየተቧደኑ የየራሳቸው የጎበዝ አለቃ አይነት መስርተው ይኸው ዛሬ ድረስ ኢራቅ ሰላም እየናፈቃት የሃብታም ደሃ ሆና አለች።
በቅርቡ ራሳቸው የትህነግ አመራሮች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰራዊት እንዳላቸው በቃል፣ በሰላፍ ትርዒትና በመረጃ አሳይተውናል። ይህ ሰራዊት ከዘረፈው ትጥቅ ጋር ሲዳመር እጅግ ዘመናዊ የሚባል መሳሪያ የታጠቀ ነበር። ከዚህ ግዙፍ ቁጥር ውስጥ አንድ አራተኛው እንኳን ብቃት ያለው ወታደር ቢሆን በዚህ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይህ ሃይል የት ገባ? ምን በላው? ተደመሰሰ? ተማረከ? ወይስ ምን ሆነ? ከማይከድራ ጅምላ ጭፍጨፋ በሁዋላ ሱዳን የመሸገው ሃይል እሱ ብቻ ነው?
ይህ ጥያቄ በወጉ ሊመልስ ስለሚገባው ከላይ የጠቀስናቸውን ወገኖች ምስክርነት ተቀብለናል። እንደ ምስክሮቹ ገለጻ ላለፉት ሁለት ዓመታት የተገነባው ሃይል ጦርነቱ ሲጀመር በአብዛኛው የወታደር ልብሱን እየጣለ ወደ መኖሪያ ቀዬው ተመልሷል። መከለከያ የማያውቀው ካፍ እሰገደፉ መሳሪያ የታጨቀበት ግምጃ ቤት በመቀሌ ከተማ ሲገኝ አንድ ከፍተኛ መኮንን ይህንን ደግመውታል። ከግምጃ ቤቱ ውጪ የወዳደቀ ልብስና ፈንጂ እያመላከቱ ” ሰራዊቱ ሲፈረጥጥ ጥሎት የሄደው ነው” ብለው ነበር።
በስራ እዛ በነበሩበት ወቅት ከአከራዮቻቸውና በጊዜ ርዝመት ከተግባቧቸው በቀጥታም ባይሆን በተዛዋሪ ያረጋገጡት ነገር ቢኖር በግልጽ በማይታወቅ ምክንያት የትህነግ ሃይል ሸሽቶ ወደ ቤቱ ነው የገባው። መሳሪውን ይጣል አይጣል ግን አይታወቅም።
በመቀሌ ባንክ ይሰራ የነበር አንድ ጸሃፊ “መቀሌ ስትያዝ “ጦርነት ላማረው ና በለው” በሚል ርዕስ እንዳለው እድሚያቸው 14 የሚሆን ልጆች መቀሌ ከተማ ከመያዟ አንድ ቀን በፊት ክላሽ ታጥቀው ወደላይ እየተኮሱ ሲሳሳቁና እንደ ርችት በተኩስ ድምጽ ሲዝናኑ እንደነበር መስክሯል። እነዚህ ታዳጊዎች ስጋት ባይሆኑም ልዩ ሃይል የሚባለውና ሚሊሻው ግን ስጋት ሊሆን ይችላል።
አሁን ድረስ ” በለው” የሚሉትና እንደ ሮይተርስ ባሉ ሚዲያዎች ተስፋ እየገመጡ ያሉ አፍቃሪ ትህነጎችና ተከፋይ ቅምጥ ጋዜጠኖች ይህን ሃይል ይሁን ሌላ ባይታወቅም በቅርቡ ጦርነት እንደሚጀመር ለመግለጽ ይሞክራሉ። ሃሳቡ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም፣ አዲሱ አስተዳደር ግን ለአፍታም ቸል ሊለው የማይገባ ሃቅ አለ።
አዲሱ የትግራይ አስተዳደር 
አዲሱ የትግራይ ጊዜያው መሪ ዶ/ር ሙሉ ነጋ ትናንት ለሚዲያ እንደገለጹት አዲስ በሚቋቋመው የትግራይ ካቢኔ ውስጥ የተቃዋሚ አመራሮች ተሳታፊ እየሆኑ ነው። ካቢኔ ሆነው የተሾሙም አሉ። በዚህ መልኩ አዲሱ አስተዳደር እየተዋቀረ ሲሆን በታችኛው እርከን ህዝብ የፈለጋቸውን እየመረጠ መሆኑንንና ይህም በትግራይ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሆነ ነው።
” ህግ ማስከበሩ ሲጀመር እንደምናሸንፍ ስንናገር ያመነን አልነበረም። ግን አደረግነው። አሁንም የትግራይ ሕዝብ በፍጹም ነጻነት በሚፈልጋቸው መሪዎቹ እንዲመራ አድርገን ታሪክ እናስመዘግባለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ይህ ልክ ህግ ማስከበሩ ሲጀመር እንደሆነው ህዝብ ላያምን እንደሚችል ጠቁመዋል። አያይዘው ግን ” ይህ መንግስት ያለውን ያደርጋል። እናደርገዋለን” ሲሉ ነው መቀሌ ሆነው ለአዲሱ አመራር ቃላቸውን ያረጋገጡት።
እንደሚሰማው ከሆነ ለጊዜው ዝርዝር ማቅረብ አልተፈለገም እንጂ በትግራይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሊባሉ የሚችሉ በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ እየተካተቱ ነው። እነዚህ ከወራት በፊት ከትህነግ ጋር የምርጫ አሟሟቂ ሆነው ተሰልፈው በዜሮ ተሸነፉ የተባሉ ፓርቲዎች ጥያቄው ቀርቦላቸው ትግራይን ወደ ዴሞክራሲያዊ ጎዳና ለመምራት እየተሳተፉ ናቸው።
ይህ መልካም ቢሆንም ልክ የሶማሌ ክልል መሪ አቶ ሙስጣፊ እንዳደረጉት የትግራይ ፖሊስና ሰላማዊ የልዩ ሃይል ወደ ስራው ሊመለስ የሚችልበት ሁኔታ ሳይውል ሳያድር ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ዘሮም ያምናል። የዘወትር የዛጎል ተባባሪና የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ እንደሚለው ይህ ተገፍቶና አንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲያይ የተደረገ ሃይል ከተገፋ በአዕምሮው ውስጥ ያለው የስሃተት ትምህርት ሁሌም ጦርነት ናፋቂ ያደርገዋል። ደሞዝ ስለለመደ ሲጓደልበት ወደ ነውጥ መግባቱ አይቀርም።
አሻግሬ ዮሃንስ የዘሮም የሙያ ባልደረባ ሲሆን ሃሳቡን ይጋራል። ይቀደመውን የጸጥታ ሃይል በተራ የፖሊስ ትጥቅ ወደ ስራ መመለስ ትግራይን ሰላም እንደሚያደርጋት ያምናል። ወደ ስራ መልሶ ልቡናውንና አዕምሮውን በማከም ጤነኛ ማድረግ እንደሚቻልም ይጠቁማል። እሱ እንደሚለው አዲስ አስተዳደር ከዚህ አንጻር ብዙ ስራ ይጠበቅበታል። ይህ ከሆነ የመከላከያንም ስራ ያቀላል።

የትግራይ ምሁራን የት ናቸው?

More than 1 million displaced in Ethiopia's Tigray region as UN warns of 'critical' food shortages
አንዳንድ እጅግ ጥቂት የሚባሉ የትግራይ ተወላጅ ምሁራን ቀደም ብለውም ቢሆን እንዲህ ያለው ጉዳይ እንዳይመጣ ሲመክሩ እንደነበር ይታወቃል። አብዛኞቹ ግን ” ትህነግ ወይም ሞት” በሚል ሙቀት ውስጥ ሆነው ዲፋክቶ መንግስት እንዴት እንደሚመሰረት ሲያማክሩና፣ የዲፋክቶ መንግስት መተዳደሪያ ሲያረቁ ነበር።
ትህነግ ምን ያህል ዝርፊያና ሌብነት ውስጥ እንደተዘፈቀ፣ በዘመድ አዝማድ ተተብትቦ የግለሰቦች ስብዕና ላይ የተገነባች ትግራይን መስርቶ ድሆችን እንደዘነጋ፣ ከወሃ አቅም እንኳን ያረረበት ሕዝብ እንደሆነ፣ ሙስናና ፖለቲካዊ ምንዝርና እንደሚፈጸም እየተረዱ ዝምታን መምረጣቸው እጅግ አነጋጋሪ ነበር። ይባስ ብለው በገሌ ቁስል እንጨት ስደድበት አይነት ” አዲስ አበባ ሄደን መንግስት አውርደን እንመለሳለን” እያሉ የሚያቅራሩ የተማሩ መሃይሞችም የታዩበት ነበር።
እንደ ምሁር በግራ አማራን የሚያክል ነካከተው ነካከተው አውሬ ያደረጉት ሃይል፣ በላይ ሻዕቢያ የሚባል ክህደት ተፈጸመብኝ የሚል ኮብራ፣ በዚህ በኩል ከመላው የኢትዮጵያ መንግስት ጋር ግጭት ውስጥ የገባው ትህነግ አካሄዱ እንደማያዋጣው በመጠቆም ወደ ጦርነት እንዳይገባ ከመምክረ አንጻር ብዙም እንዳልሰሩ የሚያውቁ ይወቅሷቸዋል።
ዛሬ ግን ነገሮች ስለተቀየሩ ትግራይና የትግራይ ምስኪን ሕዝብ መከራው እንዲቆም ቢያንስ ንጹህ ውሃ የሚያጠጣው መንግስት እንዲበጅለት በቀናነት ሊሳተፉ፣ ከጎረቤታቸው አማራ ሕዝብ ጋር ልዩነታቸውን በማስታረቅ ሰላም እንዲሰፍን ሊሰሩ እንደሚገባ፣ እንዲሁም በጅምላ ለተጨፈጨፉ ዜጎች ድምጽ ሊሆኑ እንደሚገባም የሚወቅሷቸው ይጠይቃሉ።
በትግራይ ክልል የተጀመረው የሽግግር ሂደት በክልሉ የዴሞክራሲ መሰረት የሚጥል እንደሆነ የጊዜያዊ አስተደዳሩ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ በተደጋጋሚ እየተናገሩ በመሆናቸው ለዚህ ስኬት ተባባሪ ሆኖ ሕዝብ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን አጋዥ ሃይል ሊሆኑ እንደሚገባ የበርካቶች እምነት ነው። ይህ ሲሆን ነው ትግራይ ከዛስ የሚለው መልስ ምላሽ የሚያገኘው።
ሌሎች በትግራይ ሕዝብ ምርጫ አትግቡ
ዘሮም እንደሚለው አሁን ያለው ትልቁ ችግር ጣልቃ ገብነት ነው። ካሁን በሁዋላ ምርጫው የትግራይ ሕዝብ ስለሆን የትግራይ ሕዝብ በሚወስነው ጉዳይ ጣላቃ ገብቶ መፈትፈት ያለቀው የህግ ማስከበር ዘመቻ በህዝብ ጭንቅላት ውስጥ ተቀብሮ ሲፈልግ የሚፈነዳ ማድርገና የአገር መከላከያ ሃይል የከፈለውን መልከ ብዙ መስዋዕትነት አፈር ማብላት ነው።
ብሽሽቅን፣ አጉል ዘራፍ ባይነትንና ልክ ትህነግን መቀመቅ እንደከተተው አይነት ቀረርቶ በማቆም አስተውሎ ቀጣዩን ጊዜ ውብ ለማድረግ ከትህነግ ስህተት መማር አስፈላጊ ይሆናል። ገዳይም ሟችም ወንድም በሆነበት፣ በርካታ ለመስማት የሚቀፉ ወንጀሎች በሚሰሙበትና ገና ብዙ ጉድ እንደሚወጣ በሚጠበቅበት ሁኔታ ስሜትን መቆጣተር ካልተቻለ አደጋ ይኖረዋልና እንተንቀቅ!!

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ወርቃማ ድል የተጎናጸፍነው ትልቁን ስዕል ማየት የሚችሉ ፣ ችግሮቻቸውን የመፍታት ልምድ ያላቸው እናትና አባቶች ስላሉን ነው – ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *