የተወለዱትና ያደጉት በቀድሞው አጠራር በከንባታና ሃድያ አውራጃ እንደጋኝ ክፍለህዝብ በሚባል አካባቢ ነው። ይህ አካባቢ ከጉራጌ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች አንዱ ነው። ፊደል የቆጠሩት በዚያው አካባቢ በሚገኝ የቄስ ትምህርት ቤት ሲሆን መራቢቾ እና ሙርሲጦ በተባሉ ትምህርት ቤቶች የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል።

በመቀጠልም ሆሳዕና ዋቸሞ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ገብተውም በጂኦግራፊና ታሪክ ትምህርቶች ዲፕሎማቸውን ያዙ። ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በወሎ ክፍለሃገር ኮረም ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት ካስተማሩ በኋላ ተወዳድረው የነፃ የትምህርት እድል አግኝተው ራሺያ ይሄዳሉ። በራሺያም በካርታ ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውንና የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሰሩ።

በ1984 ዓ.ም ወደአገራቸው ከተመለሱ በኋላ ደቡብ ክልል ሃዋሳ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ቅየሳና ካርታ ንድፍ ክፍል ኃላፊ ሆነው ለአራት አመታት አገለገሉ። በመቀጠልም በቀድሞ አጠራር የናዝሬት የቴክኒክ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የአሁኑ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለሰባት አመታት ካገለገሉ በኋላ በዚያው የትምህርት መስክ ዶክትሬት ዲግሪያቸውን ለመስራት ዳግመኛ ወደ ራሺያ ተጓዙ።

ተምረው ከመጡ በኋላ ግን ለረጅም ጊዜ ያገለገሉበት የትምህርት ክፍል ያለበቂ ምክንያት ተዘጋና ለምን ብለው በመሟገታቸው ምክንያት ከስራ ተሰናበቱ።ከአንድ ዓመት በላይ ተሟግተው ወደ ስራ ተመለሱ። በአሁኑ ወቅትም በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

እንግዳችን ዶክተር ኢንጅነር ጥላሁን ኤርዱኖ በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ አድርገዋል። እንደሚከተለው ይቀርባል።

አዲስ ዘመን፡– በአንድ ፅሑፍ ላይ ለረጅም ጊዜ ካገለገሉበት የአዳማ ዩኒቨርሲቲ በግፍ መባረርዎትን የሚገልፅ ሃሳብ አስፍረዋል። እስቲ ስለዚህ ጉዳይ ምንነት ለአንባቢዎቼ ያብራሩልኝና ውይይታችንን ብንጀምር?

/ ኢንጅነር ጥላሁን፡ ይህ የሆነው በ2008 ዓ.ም በምሰራበት ተቋም ውስጥ የተለያዩ ችግሮች ተፈጥረው ከስራ እንድወጣ ተደርጌ ነበር። በአሁኑ ወቅት ምንም እንኳን ወደ ስራ ገበታዬ ብመለስም በወቅቱ የእኔ ባልሆነ ችግር ከስራዬ ያለምንም ማስጠንቀቂያ እንድሰናበት በመደረጉ ብዙ ችግሮችን እንዳሳልፍ ሆኜአለሁ። ይኸውም ከ20 የትምህርት መርሐግብር ውስጥ 12 ብቻ ይቀጥሉ ሲባል በዚያ ሂደት ውስጥ ቀሪዎቹ ትምህርት ክፍሎች እንዲዘጉ ተደረገ።

ይህ ሲሆን ግን የተዘጉት ትምህርት ክፍሎች አመራሮችም ሆነ መምህራን በአጠቃላይ በዚያ ክፍል የሚሰሩ ሠራተኞች ሁሉ በሚገባ እንዲያውቁ አልተደረገም ነበር። በሁለተኛ ደረጃ በምን መስፈርት እነዚያ ስምንት የትምህርት ክፍሎች ተነጥለው እንዲዘጉ ተደረጉ የሚለው ነገር ግልፅ አይደለም። በወቅቱ እኔ ለምን እንደተዘጉ ግልፅ እንዲሆንልኝ ጠየኩኝ። ይሁንና ይህን ጥያቄ ማንም በትክክል ሊመልስልኝ አልቻለም። የሚሰጠውም ምላሽ ትክክለኛ አልነበረም።

ይህንን ተገን አድርጎ በተደረጉ ንግግሮች ውስጥ ያለመግባባቶች ነበሩ። ከዚያ ጋር በተያያዘ ውይይት ነበር። ከክልል የመጡ ኃላፊዎች በነበሩበት ውይይት ላይ ማን ትክክል እንዳልሆነ፤ ማን ጥፋተኛ እንደሆነ ተናገርኩኝ። ይሄ ንግግር እንደመጥፎ ንግግር ተደርጎ ተወስዶ ከሥራ እንድወጣ የተደረኩበት ሁኔታ ነበር።

ከዚያ ጋር ተያይዞ የመጨረሻ ችግር ፈጣሪ የነበረውና በአሁኑ ወቅት በሕግ ጥላ ሥር ያለው ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ነበር። ይህ ሰው በወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ኃላፊ ነበር። ቦርዱ ሳይሰበሰብ ብቻውን በእኔም ሆነ በሌሎች ላይ የተወሰነው ውሳኔ ሕገወጥ በመሆኑ በይፋ ነበር የተቃወምኩት።

ይህ ግለሰብ በሕጉ መሰረት የዩኒቨርሲቲውን ውሳኔ መጨረሻ ላይ የሚያየው ቦርዱ እንደመሆኑ ለቦርዱ አቅርቦ ከማስወሰን ይልቅ ራሱ ብቻውን የወሰነውን ውሳኔ ቦርዱ እንደወሰነ በማስመሰል አድርጎ ነው ያለምንም በቂ ምክንያት ከሥራ እንድሰናበት ያደረገው።

ይህም እኔ እንድከሳቸው ምክንያት ሆነ። የሚገርምሽ ከዘጠኝ ጊዜ በላይ ቢሮው ብመላለስም አንድም ቀን ላገኘው አልቻልኩም ነበር። የቦርዱን ውሳኔ እንዲያሰጠኝ የጠየኩትንም ጥያቄ ሊመልስልኝ አልቻለም። በዚህ የተነሳ ለእምባ ጠባቂ ከሰሥኩት።

እምባ ጠባቂ እንደተቋም ለቦርዱ ማመልከቻ ሲፅፍ ለቦርዱ ሰብሳቢ ተብሎ መፃፍ አለበት ብሎ ደብዳቤውን መለሰው። በዚህ መልኩ ሲያስገድዳቸው እምባ ጠባቂ የተቋሙ አመራሮች ከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ ገብተው ነበር።

ሰውዬው ለካ እግዚአብሄርም የማያዘው ግትር ነበር። በመሆኑም እሱ ባለው መልኩ እንደገና ተፃፈለት። ይታይሽ እንግዲህ በህጉ መሰረት አንድ ተቋም ለተቋም ወይም ለቦርድ እንጂ ለግለሰብ የመፃፍ ግዴታ የለበትም። ይህ ማለት በሌላ አነጋገር እኔ የተባረርኩት ቦርዱ ተሰብስቦ ወሰኖ አፅድቆ እንዳልሆነ ስለሚያውቅ ብቻውን ምላሽ እንዲሰጠው ከማሰብ እንደሆነ ግልፅ ነው።

ጄኔራል ክንፈ ብቻውን ባስተላለፈው ትዕዛዝ መሰረት እምባ ጠባቂው ለቦርዱ ሰብሳቢ ብሎ እንዲፅፍለት ተደረገ። ይህም ማለት እምባ ጠባቂው ለአንድ ግለሰብ ታዛዥ ሆነ ማለት ነው። እኔ ግን በዚህም ሳልወሰን የተሰጠኝን መልስ በመያዝ ዳግመኛ ሲቪል ሰርቪስ ፍርድ ቤት ከሰስኩኝ። ከአንድ አመት በላይ ከተከራከርኩ በኋላ ጉዳዬ አልቆ ምንም ጥፋት እንዳልሰራሁኝ ተረጋግጦ ወደ ሥራዬ ለመመለስ ችያለሁኝ።

አዲስ ዘመን – ካሳ ተከፍሎዎት?

ዶ/ር ኢንጂነር ጥላሁን፡- በፍፁም! ወደ ስራዬ እንድመለስ ብቻ ነው የተፈረደልኝ። የተወሰነው ውሳኔ ግን በጣም የሚያስገርም ነው። ምክንያቱም አንድም ነገር በእኔ ላይ ማግኘት አልቻሉም።

ይልቁንም ከስራ መባረር ቀርቶ ሊያሸለም የሚገባ ተግባር መፈፀሜን ነው ከሰነዴ የተረዱት። ለምን ተነጋግረን ችግር አንፈታም? ነበር የእኔ ብቸኛ አቋም የነበረው። የማልዋሸው ነገር በዚህ ውሳኔ በጣም ተናድጃለሁ፤ ስሜታዊም ነበርኩ። ከዚያ ውጭ ሊያስባርር የሚያስችል ምንም ጥፋት አልነበረብኝም ነበር።

ምክንያቱም የዲፓርትመንቱ አባላት ሳያውቁ ምንም አይነት የትምህርት ከፍል መክፈትም መዝጋትም የማይቻል በመሆኑ ነው። በነገራችን ላይ ትልቁ የዩኒቨርሲቲ ሥራ ያለው ዲፓርትመንት ውስጥ ነው፤ ተማሪም ሆነ መምህር እንዲሁም ካሪኩለም ያለው እዚያ ነው።

ይህንን ዋነኛ ባለድርሻ አካል ባይተዋር አድርገው ነው እንግዲህ በአንድ ግለሰብ ውሳኔ ዲፓርትመንቱ እንዲዘጋ ያደረጉት።

በኋላ ላይ እንዳውም እንደሰማሁት ይህ ግለሰብ ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ቢሆን እንደማይታዘዝ ነው።

አዲስ ዘመን፡– ከተማሩት ሙያ ውጭ ብዙ ጊዜ በተለያዩ ጋዜጦች ላይ አስተማሪ ፅሑፎችን ይፅፋሉ  ይሳተፋሉ፤ ለዚህ የተለየ ምክንያት አለዎት?

ዶ/ር ኢንጅነር ጥላሁን፡- እኔ ከቄስ ትምህርት ቤት ጀምሮ ለሰንደቅ ዓላማና ለአገሬ ፍቅር እንዲኖረኝ ተደርጌ ነው የተቀረፅኩት። በተለይም ለአገሬም ያለኝ ልዩ ፍቅር ከፍተኛ በመሆኑ ስለሃገሬ በተነሳበት ጊዜ ሁሉ እምባዬ ይመጣል። በዚህ የተነሳ ብዙ ችግር ደርሶብኝም ያውቃል።

በተለይም ህወሓት የሚባለው ድርጅት አገር ወዳድ በመሆኔ ብቻ ቀላል የማይባሉ ጫናዎች አድርሶብኛል። በነገራችን ላይ ይህንን የወንበዴዎች ቡድን የማውቀው ከ1976 ዓ.ም ወሎ ኮረም እሰራ ከነበርኩበት ጊዜ ጀምሮ ነው።

በዚህች አገር ላይ የሚዶለተውን ነገር በቅርብ ርቀት እመለከት ነበር። የታሪክም ተማሪ ስለሆንኩኝ ከታሪክ ጋር የሚጋጭ ነገር ነው እያየሁኝ የኖርኩት። ይህንን ማለፍ አልቻልኩም። ምክንያቱም ሁልጊዜ የሚጋጭ ነገር ነበር የማየው። የነበረን ዓለምን የሚያስደንቀውን ታሪካችንን እየተውን የሌለ አዲስና ማንም ሊያዳምጠው የማይችል፤ ለማንም ትርጉም የማይሰጥ ታሪክ ለመፍጠር ነበር ትግል ሲያደርጉ የኖሩት።

ይህን ታሪክ የማጠልሸት ሂደት ለመግታትና ትውልዱ ትክክለኛውን እውነታ እንዲረዳ ለማድረግ ስል የግሌን ጥረት አደርግ ነበር።በተለይም በምሳተፍባቸው መድረኮች ሁሉ የተያዘው አካሄድ ትክክል እንዳልሆነ አነሳለሁ።የምሰጣቸው አስተያየቶችና የምጽፋቸው ፅሑፎች የፖለቲካ ታፔላ ይለጠፍባቸው ነበር።

ትክክለኛ ሥራ ሰርቶ ለትውልዱ ሥራ ከመፍጠር ይልቅ በአልባሌ ነገር የወጣቱ አዕምሮ እንዲያዝ ነበር የሚደረገው። ይህም ትክክል እንዳልሆነ በየአጋጣሚው እገልጻለሁ። በተለይም በማህበራዊ ሚዲያውም ሆነ በአንዳንድ ጋዜጦች ላይ ለአገር ይጠቅማል ብዬ በማስባቸው ጉዳች ላይ እፅፋለሁኝ።

በተለይም የአገሪቱ ቁልፍ ችግር የጦርነት ታሪክ ችግር ነው የሚል እምነት ሥላለኝ ትውልዱ ሥለ ኢትዮጵያ ስትራቴጂክ የሆኑ ታሪካዊ ጠላቶች አላማ እንዲረዳና አገሩን ከጥቃት መታደግ አለበት የሚል አንድምታ ያላቸውን ፅሑፎች እፅፋለሁኝ።

ይህንን ነገር በደንብ እንዳስብበት ያደረገኝ ደግሞ ራሺያ ለትምህርት በሄድኩበት ወቅት በአንድ ሶሪያዊ ተማሪ አማካኝነት መላው የአረብ አገራት ኢትዮጵያ ላይ የተለየ ምልከታ እንደነበራቸው፤ በተለይም የአባይን ውሃ እንዳትጠቀምበት ለማድረግ ሲሉ በአገሪቱ ላይ ትርምስ እንዲፈጠር ለማድረግ ያደርጉት የነበረውን ጥረት ለማወቅ ችያለሁ።

በተለይም በደርግ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ኤርትራ እንድትገነጠል የነበረውን አሻጥር ያ ሶሪያዊ ይነግረኝ ነበር። አሁንም ቢሆን እነዚህ አገሮች እኛን ለመበታተን እንደማይተኙ ስለማውቅ ትውልዱ እንዲያውቅና እንዲገነዘብ ሥል የተለያ ፅሁፎችን እፅፋለሁኝ።

በነገራችን ላይ ግብፅን ጨምሮ ከሌሎችም የአረብ አገራት ሁልጊዜ ኢትዮጵያን የሚጠቀሙበት ቀጭን ክር አለች። እሷም የውስጥ ችግር ነው።

ታሪክን መለስ ብለሽ ካየሽ ለአፄ ቴዎድሮስ መገደል ምክንያት የሆነው እርስ በእርስ ችግር ነው። አፄ ዮሐንስ የእንግሊዙ ጦርን አሳልፈው መስመር አስተው አፄ ቴዎድሮስን እንዲመቱላቸው ባያደርጉላቸው ኖሮ አፄ ቴዎድሮስ ጠቅላላ ኢትዮጵያን ከምኒሊክ በፊት ያገናኙት ነበር።ስለዚህ የውጭ ጠላት ሁልጊዜ የሚደፍረን በደካማ ጎናችን እየገባ ነው።

እናም ይህንን ታሪክ እንዳጠና ያደረገኝ ያ ሶሪያዊ ነው። ይህ በእኔ እድሜ ያለ ይኸው ሰው እንደነገረኝ እነዚህ አረብ አገራት የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለ ለሻዕቢያ ጦርነት ያዋጡ ነበር። እነዚህ አካላት ለሻዕቢያ ደግፈው ስትራቴጂክ ወንድሞቻችንን አሳጥተውናል። ለመገንጠላቸው መሰረታዊ ምክንያት ደግሞ እነሱም እኛም አይደለንም። ዋነኛው መንስኤ ኢትዮጵያን የማዳከም ፍላጎት በውጭ ኃይሎች ይታሰብ ስለነበረ ነው።

ይህም ኢትዮጵያ ባላት የተፈጥሮ ሃብትን እንዳትጠቀም የማድረግ ከንቱ ፍላጎትና ሥጋት የመነጨ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሠላም ካገኘች ልማት ታስባለች፤ ለመልማት ስትፈልግ ደግሞ ውሃ ትገድባለች የሚል መነሻ ስለነበራቸው ነው።ይህ አይነቱ ደግሞ ስጋት ያላቸው ግብፅና ሱዳን ብቻ አይደሉም።

ሱማሊያም ጭምር እንጂ። ምክንያቱም ደግሞ ወደ ሱማሊያ የሚፈሱት አብዛኞቹ ወንዞች ምንጭ ኢትዮጵያ በመሆንዋ ነው። ያን ጊዜ በዚያ ሶሪያዊ ትንኮሳ ምክንያት የአረብ አገራትን ሴራና ታሪክ ለመመርመርና ለማጥናት ተገድጅለሁ። እናም ከዚህ ያገኘሁትን እውቀት ነው ለማካፈል ጥረት የማደርገው።

አዲስ ዘመን፡– ይህ ትውልድ ታሪክ በቅጡ አልተረዳም ለማለት መነሻዎት ምንድን ነው?

ዶ/ር ኢንጅነር ጥላሁን፡- ይህ ትውልድ ለ30 ዓመታት ውሸት እየተነገረው ነው የኖረው። ታሪካዊዎቹ ጠላቶቻችንም ታሪክ እንዲያውቅ ከማድረግ ይልቅ እርስ በርስ እንዲባላ ነው ያደረጉት። ለዚህ ደግሞ ህወሓት ሰራሹ አመራር ነው ተጠያቂ ሊሆን የሚገባው።

በነገራችን ላይ በእኔ አረዳድ እዚህ አገር አምስት የህወሓት ጁንታዎች ናቸው ያሉት። አንደኛው ጁንታ አራቱን ድርጅቶች ፈጥሮ መቀሌ የሄደው ነው።

አራቱ ጁንታዎች አሁንም እዚህ አሉ። ምንም አልሆኑም። ሁለተኛው ህወሓት ከከፍተኛ ባለስልጣናት ውስጥ ያለ ነው። ይህ ኃይል አሁንም በውስጥ ሆኖ በአካባቢው ግጭቶች እንዲነሱ፣ ሙስና እንዳይቆም፣ አለመረጋጋት እንዲቀጥልና ለውጡ ወደፊት እንዳይሄድ እያደረጉ ያሉ ናቸው። ሶስተኛው ደግሞ ልማታዊ ባለሃብት የሚባሉ ፎርጅድ ባለሃብቶች ናቸው። እነዚህ ደግሞ በሂደት ከመሬት ተነስተው ሰርተው ሃብት ያፈሩ አይደሉም። ለውጡ ሥጋታቸው የሆኑ ልማታዊ ባለሃብቶች አመፁን በገንዘብ በመደገፍ ለውጡን የሚያደናቅፉ ናቸው። ሌላኛው ጁንታ ደግሞ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጀምሮ እስከቀበሌ የተዘረጋ መዋቅር አለ። አሁንም አልፈረሰም፤ የለውጥ ችግር ሆኖ እንደቀጠለ ነው ያለው።

በተለያየ መልኩ ጥቅሙ የሚነካ የመንግስት ባለሥልጣን አለ። ይህም በመንግስት ሰራተኛ ሥም በየተቋሙ የተሰገሰገ ነው። ሌላው ደግሞ ህወሓት ህብረተሰቡ ለራሱ ጥቅም ሲል በአምሳሉ የሰራው ደህንነት ነው። እሱም አልፈረሰም።

ዘረኛው ፖሊሲ ሌላኛው የጁንታው ሴል ነው።የሰው ህይወት እየጠፋና ሃብት እየወደመ አልታዘዝንም የሚል ማለት ነው። ሰው እየተገደለ ግለሰብ አንጠብቅም የሚል አሳፋሪ ምላሽ ይሰጣል። ይህ ሁሉ ችግር ባለበት ዝም ብሎ መቀመጥ ከባድ ስለሆነብኝ ነበር የበኩሌን አስተዋፅኦ ለማበርከት ጥረት ያደረጉት።

አዲስ ዘመን፡– በሚፅፏቸው ፅሁፎችና በሚሰጡት አስተያየት በግልዎ የደረሰብዎት ነገር አለ?

ዶ/ር ኢንጅነር ጥላሁን፡- ልክ ነሽ፤ አንድነት ለኢትዮጵያ የውዴታ ጉዳይ ሣይሆን ግዴታ ጉዳይ ነው በማለቴ ብቻ ብዙ ጊዜ በሚኒስትሮች ሳይቀር ተሰድቤያለሁ። ኢትዮጵያ ከአንድነት ውጭ መኖር አትችልም ብዬ ስናገር ደማቸው የሚፈላ ሚኒስትሮች ነበሩ። በበርካታ ስብሰባዎች አሸማቀው የሚያስወጡኝ ጊዜ አለ።

በነገራችን ላይ አሐዳዊ አስተሳሰብ ነው ቢሉም እንኳን አሐዳዊ ስለሚሉት ቃል እንኳ በቅጡ አያውቁትም። አሐዳዊ ስርዓት የሚባል ነገር በዓለም ላይ የለም። ጨቋኝ ስርዓት ቢባል ልንግባባ እንችል ይሆናል።

ባለሥልጣናቱ የራሳቸውን እድሜ ለማራዘም ሥርቆታቸውን ለማስቀጠል እንጂ ለሕዝቡ አስበውለት አይደለም። ህወሓት ለብሄረሰቡ ያዘነ በመምሰል የቡድን መብት አስከብራለሁ እያለ በሃሰተኛ ትርክት አገር ሲገዛ ነው የኖረው።በቡድን መብት ውስጥ የግለሰብ መብት የለም። የግለሰብ መብት ከተከበረ ግን የቡድን መብት እንዲከበር እድል ይሰጣል። እነሱ ይህንን አይቀበሉም።

አዲስ ዘመን፡– በለውጡ ሂደት ያሉ መልካም እድሎችና ሥጋቶች በእርሶ እይታ ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ኢንጅነር ጥላሁን፡- ከለውጡ ማን ይጠቀማል ከሚለው ብንጀምር ደስ ይለኛል። በእኔ እይታ ከለውጡ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተጠቃሚ ነው። ሕዝብ ተቃውሞና ከውስጥ በነበረው ብርቱ ትግል ነው ዛሬ እንደልብ የምናጣጥመውን የነፃነት አየር መተንፈስ የቻልነው። ከዚህ አንፃር እንግዲህ ለውጡን የሚገዳደሩ ነገሮች አንደኛው ህወሓት ነበር።

አሁን እሱ ከሞላ ጎደል በእኔ እይታ መልክ እየያዘ ነው። ከዚህ ውጭ አስቀድሜ የዘረዘርኩዋቸው እሱ የፈጠራቸው የለውጥ እንቅፋቶች አሉ። እነዚህን አራቱ የህወሓት ጁንታ ሰራሾችን መታገልና ወደ መስመር ማስገባት አሻፈረኝ ያለውን ወደ እስር ቤት ማስገባት ነው የሚገባው። ለውጡ በአጭር ጊዜ ወደ መስመር ይግባ ከተባለ ያጠፋ በሙሉ ተገቢውን ቅጣት ማግኘት ይገባዋል። ያላጠፋው እንዲሰራ መደገፍ ይገባል። እነዚህን ኃይሎች ሥርዓት ማስያዝ ያስፈልጋል።

መንግስት መልዓክ ሊሆን አይችልም። መንግስት ፈረንጆቹ እንደሚሉት ካሮትና አርጩሜ መጠቀም ይገባዋል። ሁሉንም ክልሎች እኩል ማስተዳደር ያስፈልጋል።

የሚበጠብጥ ካለ መምከር ፤ ቶሎ ማጣራት ያስፈልጋል። አልመከር ካለና በተሳሳተ መንገድ የሚቀጥል ከሆነ ለፍርድ ማቅረብ ያስፈልጋል።ስለዚህ ካሮቱና አርጩሜው አብሮ መጓዝ አለበት የሚል አቋም ነው ያለኝ።

ይህንን የማነሳው ወድጄ አይደለም። በጣም ከፍተኛ የሆነ ትእግስት ነበረ። በጉራጊኛ አንድ ተረት አለ። አንድ ሰው በተለያየ ቦታ እሳት አቃጥሎታል። ‹‹ እዚህ ጋር ምን ሆንክ›› ሲሉት ‹‹እሳት አቃጠለኝ›› ይላል፣ እዚህስ ጋር ሲሉት እዚህም ጋር እሳት ይላል።

‹‹እንዲህ ሁሉ ቦታ እስኪያቃጥልህ አንተ የት ነበርክ?›› አሉት ይባላል። እናም ትእግስት ሁል ጊዜም አይደለም የሚሆነው። በሕዝባዊ አመራር ከሆነ አርጩሜና ካሮቱን ሚዛን አስጠብቆ መጓዝ ያስፈልጋል። ስለዚህ አሁንም የለውጡ ተግዳሮት ቅድም የዘረዘርኳቸው አምስት አይነት ችግር ፈጣሪዎችን እየለዩ ስርዓት ማስያዝ ይጠይቃል። ለአገር የሚበጀውን ከማስተማር ጀምሮ ለፍትህ እስከማቅረብ ድረስ ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡– ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ላካሄደችው የመሬት ወረራ መፍትሔው ምንድን ነው ተብሎ ይታመናል?

ዶ/ር ኢንጅነር ጥላሁን፡- መፍትሔ አለው። መፍትሔው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። አንደኛ መሬቱ የእኛ ነው። በነገራችን ላይ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር ጉዳይ አገራቱ የተስማሙበት ድንበር የለም። ኢትዮጵያ የያዘችው መሬት አለ፤ ሱዳን የያዘችው መሬት አለ። ከእዚህ ውጭ በድንበር ጉዳይ ኢትዮጵያና ሱዳን ተስማምተው የፈረሙት ፊርማ የለም። ኢትዮጵያ የፈረመችው ከእንግሊዝ ጋር ነው።

እንግሊዝ ቅኝ ገዢ ነች። ያንን ውል ስንፈርም ደግሞ ውሎ በሚፈረምበት ሰዓት የተለያዩ እንግሊዛውያን የእዛን አካባቢ መሬት የያዙ ዜጎች ነበሩ። እነዛ ዜጎች ከእንግሊዝ ተልከው ሲመጡ ከምኒሊክ ጋር ያደረጉት ድርድር ነበር። ያ የድንበር ክርክር በተግባር ሲተረጎም ኢትዮጵያውያን ተመልካቾች እማኞች ይኖራሉ ተብሎ ነበር። እማኞች አልተገኙም ነበር።

አንድ እንግሊዛዊ ነው ካርታ ሰርቶ መስመሩን ያወጣው። ካርታ ሰርቶ በ1891፣ በ1892 ለመደራደር ሞከረ። ሲሞክር የመጨረሻ ውሳኔ የነበረው ድንበሩ በወረቀት ላይ የሰፈረው እቅድ መሬት ላይ ሲወርድ ከኢትዮጵያ ወገን ይኖራል ነው። የኢትዮጵያ ወገን አልነበረም። በወቅቱ ምኒሊክ ደግሞ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ጠረፍ ነው የሚሉት። ጠረፍ ማለት ለእርሳቸው ኢትዮጵያውያን የማይኖሩበት ቦታ ነው። ምኒሊክ እንዳውም አሁን ሱዳን ውስጥ ያለች ከተማ ድረስ ሳይቀር ነው ድንበሬ ነው የሚሉት። በእዚህ ጉዳይ የጻፉት ደብዳቤም አለ።

ስለዚህ እንግሊዝ በማያገባት ጉዳይ የገባች አገር ስለሆነች የእንግሊዝን ድንበር የምንቀበልበት ምንም ምክንያት የለም። በእርግጥ በዓለም ላይ አንድ ሕግ አለ። የቅኝ ግዛት ድንበር ይከበራል የሚል ነው። ያ ቢሆን ደግሞ ድንበር መሆኑ መሬት ላይ ሲረጋገጥ ነው። በኢትዮጵያ ድንበር ለመሆኑ ችካል ለመቸከል ኢትዮጵያውያን አልተሳተፉም። ለእዚህ ምክንያት ነበራቸው።

አካባቢው እልም ያለ በረሃ በመሆኑ ወባ የነበረበት በመሆኑ ስለሚፈሩ አልሄዱም።ሁለተኛ ደግሞ ኢትዮጵያውያን የያዙት ቦታ ነበር።ሁልጊዜ ይፈልጋሉ።

እንግሊዛዊው ያሰመረውን መስመር እንድንቀበል በአፄ ኃይለስላሴም ሆነ በደርግ ዘመን የተለያዩ ጥረቶች አድርገዋል። ግን አልተሳካላቸውም። በህወሓት ዘመን እንግዲህ ለየት የሚያደርገው በእዛ አካባቢ የድንበር ውዝግብ ድንበርን እንደገና የማሻሻያ ስራ ሲሰራ የነበረው ህወሓት ራሱ በመሆኑ ነው።

ህወሓት በትግል ዘመኑ ለሱዳን የገባው ቃል ያለ ይመስል ይህንን ለማስፈጸም ደፋ ቀና ሲል ነው የኖረው። ይህን የምልሽ ደግሞ ከመሬት ተነስቼ አይደለም። በመሬት ማካለሉ ስራ እኔ የማውቃቸው ብዙ ባለሙያዎች የተሳተፉ እንዳሉ ሁሉ አውቃለሁ።

ይህም ማለት አንደኛ እዚያ ጋር የሰፈረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደየት አድርገሽ ነው አሁን የሚሰመረው? ሁለተኛም ኢትዮጵያ አልተቀበለችውም። መሬት ላይ ሲወርድ በካርታው ላይ ምኒሊክ የፈረሙት ፊርማ አለ፤ በ1892 በካርታው ላይ። ግን ደግሞ እዛው አንቀጽ ላይ ደግሞ ምልክቱ ሲደረግ የት ጋር እንደሆነ ምልክቱ አይታወቅም። ያንን እንደ ሕግ እየጠቀሱ ተቀብለዋል ይላሉ።ለመቀበሉ ማረጋገጫ የለም።

መሬት   ሲወርድ አልነበርንም፤ እዛ አንቀጽ ላይ ስላለ ይጥለዋል። ምክንያቱም ከሁለቱም ወገን እቅዱ ወደ መሬት ሲወርድ ሰዎች ይገኛሉ ይላል። አሁን ሰበቡ ይሄ ወረራ ከግብጽ ጥቅም፣ ከሱዳን ጥቅም አንጻር ከሁለቱም ጥቅም አንጻር ማየት ያስፈልጋል።

በሌላ በኩል ሱዳንም ሆነ ሌሎች አረብ አገራት ከትግል ዘመኑ ጀምሮ ወልደው ያሳደጉት ህወሓት ሙሉ ለሙሉ እንዲሞት አይፈልጉም። ምክንያቱም ሰላም እንዲሰፍን ስለማይፈልጉ ነው። ሌላ በጣም ጽንፈኛ የሆኑ ጠላት ይፈጥሩልናል እንጂ በፍፁም አይተኙልንም።

ይሄ በግርግር መሬት እናስመልሳለን የሚል ቢሆንም ዋነኛ ዓላማው ግን ኢትዮጵያን ሰላም በማሳጣት የህዳሴ ግድባችንን ግንባታ ማስተጓጎል ነው። በርግጥ እዚህ አካባቢ ስህተት ይታየኛል። ከሱዳን ጋር የሚያዋስነን የምዕራቡን ድንበር በማናቸውም መስዋዕትነት ለሰከንድ መለቀቅ የሌለበት ነበር።

ሱዳን ሁልጊዜ መሆን የምትፈልገው ከአሸነፈው ጋር ነው። ኢትዮጵያ የፖለቲካ የበላይነቱን ስትይዝ ኢትዮጵያ ያለችውን ትቀበላለች። ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር ሲፈጠር ከግብጽ ጋር ነው የምትጎዳን።

የግብፅና የሱዳን መንግስታት ወታደራዊ ናቸው። የሁለቱም አመራሮች ወደ ስልጣን የመጡት በመፈንቅለ መንግስት ነው። ወታደራዊ መንግስቱ ኢኮኖሚውን ይዞ ነው ያለው። ከጎረቤት ጋር በሰላም መኖር አይችሉም።

ሲቪል መንግስት እንዲኖር አይፈልግም። ስለዚህ እነዚህ አገሮች ኢትዮጵያ አንድነቷን ካፀናች በምንም ተዓምር አያሸንፏትም።ግን እጃቸው ረጅም በመሆኑ ለሰላማችን መደፍረስ የሚመጡበት መንገድ አይታወቅም። ደግሞ ጎረቤት አገራትንም በጥቅም የመያዝ ልምድ አላቸው።

መልካም ግንኙነት አለን የምንላት ኬኒያ እንኳን በአባይ ጉዳይ እስከአሁን ልትፈርም አልቻለችም። ምክንያቱም ግብፅን ትፈራለች። ስለዚህ ቸል ልንላቸው አይገባም። የውጭ ጠላቶቻችንን ማሸነፍ የምንችልበትና ያለን ብቸኛ መፍትሔ የኢትዮጵያን ሕዝብ አብሮነት መመለስ ነው።

በቋንቋም ሆነ በብሔር መከፋፈላችንን ማስቀረት ይገባናል። ምክንያቱም ቋንቋ ከመግባቢያነት ያለፈ ጥቅም ኖሮት አያውቅም። እኔ ለዚህ ምስክር ነኝ። ራሺያ እያለሁ የራሺያን ቋንቋ የተማርኩት እዛ ሳለሁ ትምህርቱን ለመቀበል ረዳኝ፤ እዚህ ስመጣ ግን ከሁሉም ጋር የምግባባው በአማርኛ ነው።

ከዚያ ውጭ የተለየ ትርጉም የለውም። አንዳንድ ሊሂቃን ነን ባዮች ይህችን መሰረት አድርገው ነው የሚለያዩን።ቋንቋ እንዴት የመለያያ ምክንያት ይሆናል?። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በሙሉ የኢትዮጵያውያን ቋንቋዎች ናቸው። ለመለያየት ምክንያት ሳይሆን ሊሆኑ የሚገቡት ሊያግባቡን ነው የሚገቡት። እንዲያለያየን መፍቀድ የለብም።

አዲስ ዘመን፡– በህዳሴ ግድቡ ላይ በሚደረገው ድርድር የሱዳን አቋም መዋዠቅ ከምን የመነጨ ነው ይላሉ?

/ ኢንጅነር ጥላሁን፡ ሱዳን አቋሟ የሚዋዥቀው ከራሷ ጥቅም አኳያ ነው ባይ ነኝ። ባለፈው ታስታውሺ እንደሆነ ትራምፕ የሚባል እብድ እየሰማነው ጦርነት በእኛ ላይ ሲያውጅ ነበር።

ግብፅ በአሜሪካ እንደምትደገፍ ሱዳን ሌላው ቢቀር ትራምፕ እስከሚወርድ ድረስ የአሜሪካ ደጋፊ መምሰል ትፈልጋለች። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከእሥራኤል ጋር ሠላም አውርዳለች ፤ ምክንያቱም የአሜሪካ ወዳጅ በመሆኑዋ ለማስደሰት ሥትል ነው።

እስራኤልም የራሷ የሆነ የውሃ ጥቅም ፍላጎት አላት። ያም ሆኖ ግን እስራኤል በኢትዮጵያ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ በመግባት ሥጋት እንዲፈጠር ትረዳለች ብዬ አላስብም። ዞሮ ዞሮ ግን ሁሉም አገሮች የራሳቸውን ጥቅም ነው የሚያስቀድሙት።

በሌላ በኩል የሱዳን መንግስት ለሁለት የተከፈለ ነው። አንደኛ ወታደራዊው ሲሆን ሌላኛው ሲቪል ነው። ወታደራዊው መንግስቱ ሙሉ ለሙሉ በግብፅ ቁጥጥር ስር ያለ ነው። በነገራችን ላይ ለተወሰነ ጊዜ በግብፅ ቅኝ ተገዝታም ነበር።ስለዚህ አሁንም ቢሆን በግብፅ ተፅዕኖ ሥር ነች።

ግብፅ ቀስ በቀስ እያሳመነችና ምክንያት እየፈለገችላት ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቃረን አድርጋታለች። ይህንን ደግሞ በሰሞኑ ሁኔታ ማረጋገጥ እንችላለን። የህወሓትን መመታት ተገን አድርጋ የግዛት ጥያቄ እንድታነሳና በኢትዮጵያ ላይ ወረራ እንድትፈፅም የግብፅ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳለት ጥርጥር የለኝም። በዚህም የእኛን ጥቅም ማሳጣት ነው ዋነኛ አጀንዳቸው።

ሁለቱም የውሃ ክፍሉን ማፅደቅ ነው የሚፈልጉት። እንደሚታየው ግብፅና ሱዳን በ1959 ዓ.ም ውል በስምምነታቸው መሰረት ውሃውን ተከፋፍለውታል። ያንን ነው ማፅናት የሚፈልጉት። አሁን እኛ ይህንን ማድረግ አንችልም። ምክንያቱም የወደፊቱን ትውልድ መጪ የማደግ ተስፋ መዝጋት ስለሚሆን ነው። ስለዚህ የውሃ ክፍፍል ውስጥ አንገባም። እነሱ በውሃው ተጠቅመው እንደሚያልሙት ሁሉ እኛም የመጠቀምና የመልማት መብት አለን።

ለዚያ ችግር የእኔ የመፍትሔ ደግሞ ዛፍ መትከል ነው። ይህ ሲሆን ነው የውሃውን መጠን መጨመር የሚቻለው። እናንተ አትንኩ ከሚሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ለምን አያለሙም?። ስለዚህ የሱዳን በዚህ መልኩ መዳፈር አንደኛ በግብፅ የምትደገፍ መሆንዋ ነው። ሁለተኛ በአሜሪካም በኩል የሚደረግ ግፊት አለ። ትልቁ ጫና ግን የአረቡ አለም ተፅእኖ ነው። እንዳልኩሽ ደግሞ የኢትዮጵያ የውስጥ ችግር መባባስ የገዛ መሬታችንን እስከመውረርና እስከመተንኮስ አደፋፍሯታል።

አዲስ ዘመን፡– አንድ ወቅት በሰጡት ቃለምልልስ የአባይ ጉዳይ ለግብፅና ሱዳን የውስጥ ራስ ምታትና ችግራቸው ማስታገሺያነት እንደሚጠቀሙበት ገልፀው ነበር። አሁንም እነዚያ አገራት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር እያደረጉ ያሉት ጥረት ከዚያ ጋር ግንኙነት አለው ብለው ያምናሉ?

ዶክተር ኢንጅነር ጥላሁን፡- ትክክል ነው። እንግዲህ ግብፅ ውስጥ ዘላለሙን የመፈንቅለ መንግስት አባዜ ነው ያለው። በነገራችን ላይ ሁለቱ አገራት በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተመሰረተ ፖለቲካ አካሂደው አያውቁም።ስለዚህ የውስጥ የፖለቲካ ችግር ሲፈጠር የሕዝባቸውን ቀልብ ለመስረቅ ሲሉ ችግራቸውን ለኢትዮጵያ ይሰጣሉ።

ሁሉንም ነገር ከአባይ ጋር ይያዙታል። በሱዳን በኩልም በዳቦም ሆነ በሌላ መልኩ የሚነሳውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ለማስረሳት ሲሉ ተመሳሳይ ድርጊት ይፈፅማሉ።

አሁን ግን እሱ አይደለም ችግራቸው። የአሁኑ ሩጫቸው የራሳቸውን የውስጥ ችግር ወደጎን ትተው ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠሩትን ከባድ ችግሮች ለማባባስ ነው። የሱዳን ትንኮሳ ቸኩለን እንድንገጥማቸው ከመሻት ነው። እኛ ግን እነሱ እንደሚመኙት ቸኩለን መግጠም የለብንም። አልፈው መጥተው ከያዙት መሬት ሌላ እንዳይዙ ወጥሮ መያዝ ይገባናል።

መጀመሪያ የሚገባን የውስጥ ችግራችንን መፍታት ነው የሚገባን። በተለይ ግድቡ እየተገነባ ባለበት የቤኒሻንጉል አካባቢ ያሉ ችግሮችን በዋነኝነት መፍታት ያስፈልጋል። አሁን ከያዙት ሌላ መሬት እንዳይዙ ገትሮ መጠበቅ ያስፈልጋል። እኛ የውስጥ ችግራችንን ካቃለልን በኋላ ራሳችንን መልሰን አጠናክረን በሚገባት ቋንቋ መነጋገርም እንችላን። ይህም ለኢትዮጵያ ይከብዳታል ብዬ አላስብም።ስለዚህ ቸኩለንና ተጣድፈን ከገባን ካለብን የውስጥ ችግር ተዳምሮ አገሪቱን ወደለየለት ውጥንቅጥ ውስጥ መክተት ነው የሚሆንብን።

እንዳጠቃላይ ግብፅና ሱዳን የእነሱን የውስጥ ችግር በእኛ ላይ የሚያላክኩት ግድቡን ገንብተን እስከምናጠናቅቅ ነው።

አዲስ ዘመን፡በሌላ ቃለመጠይቅዎ ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ግድቡን ገንብቶ ማጠናቀቅ ሉዓላዊነታችንን የማስከበር ጉዳይ እንደሆነ አንስተዋል። እንዴት?

ዶክተር ኢንጅነር ጥላሁን፡- በእኔ እምነት ሉዓላዊነታችን እየተደፈረ ነው። የእኛ ችግር የጦርነት ታሪክ ችግር ነው። ዛሬ ላለንበት ድህነት አንደኛውና ዋነኛው ምክንያት የጦርነት ታሪካችን ነው።በተለይ የአረብ ሊግ አባል አገራት ግማሽ የሚሆኑት የእኛ ጎረቤቶች በመሆናቸው እነዚህ አገራት ደግሞ አባይን የሚቋደሱ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የእነሱን የመልማትና የማደግ መብት ለማስጠበቅ ሲሉ የማይምሱት ጉድጓድ የለም።

በእኛ አገር የተፈፀሙት አብዛኞቹ ጦርነቶች ጀርባ እነዚህ አገራት እጅ አለበት። አሁን ዋነኛ ስጋታቸው እኛ ውሃ ከምናጣ ኢትዮጵያ ሰላም ማግኘት የለባትም ከሚል ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሰላም ካገኘች ልማት ታስባለች የሚል ሥጋት አለባቸው።

ስለዚህ ሉዓላዊነታችንን ለማስጠበቅ ሰላም ማግኘት አለብን፤ ሰላም ለማግኘት ደግሞ ግድቡን መገንባት ይገባል። ይህንን ስናደርግ ሥጋታቸውን እንቀርፋለን ማለት ነው። የእነሱ ሥጋት ውሃ እናጣለን ከሆነ ውሃ እንደማያጡ ገድበን ልናሳያቸው ይገባል።

ካልገደብነው ትንኮሳቸዉ አይቀርልንም። ገድበን ውሃ እንደማይቋረጥ ካሳየናቸው የገዛ ሕዝባቸው ፊቱን ያዞርባቸዋል። በየጊዜው የሚሰጡትንም ምክንያት አይቀበሉትም።

አዲስ ዘመን፡– የእነዚህ አገራት ሥጋት ውሃ እናጣለን ከሚል የመነጨ ብቻ ነው ተብሎ ይታመናልበውሃውም ሆነ በቀጠናው የበላይ ሆኖ የመዝለቅ ቅጥ ያጣ ፍላጎትስ አይደለም?

ዶክተር ኢንጂነር ጥላሁን፡ ልክ ነሽ። ግን አአስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ በሁለቱም አገሮች ወታደራዊ ኃይሉ ሥልጣኑን ማስነጠቅም አይሻም።

ስለዚህ ሕዝቡ ሲነሳበት የሚያቀርበው ምክንያት ከአባይ ጋር ነው የሚያገናኙት። ሲቪሉ ስልጣን እንዳይነጥቃቸው ዘላለም አንድ ጠላት ማበጀት አለባቸው። ያም ኢትዮጵያ ነው። እንዳልሽው ኢትዮጵያ ለውጡን በትክክል ብታስቀጥልና ልማቷን ብታሳድግ ለእነዚህ አገራት ሥጋት መሆንዋ አይቀርም።

ምክንያቱም የዚህ አይነት ለውጥ እነሱ ጋር እንዲከሰት ሕዝባቸው ይፈልጋል። አሁን ግን የያዙት የፖለቲካ ጨዋታ ነው። ወታደሩ ስልጣኑን ላለመተው ሲል ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ይቀሰቅሳል። ያ አንቺ ያልሽው ሥጋት ከዚያ በኋላ አይቀጥልም ብዬ አላስብም። ቢያንስ ቢያንሥ ሌላ ሁለት ግድብ ያስፈልገናል።

አዲስ ዘመን፡– በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈ ልጉት ሃሳብ ካለ እድሉን ልስጥዎት?

ዶ/ር ኢንጂነር ጥላሁን፡- የመጀመሪያው አገር የሕዝብ ነው። ሕዝብ በአገሩ ሲኖር ደግሞ መንግሥት ያስፈልገዋል።ስለዚህ ስልጣንም አገርም የሕዝብ ነው። ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ነች። ለሕዝብ የተፈጠረች አገር ከነስልጣኑ የሕዝቡ መሆኑን አውቆ ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ ችግሮቻችንን መፍታት ያስፈልጋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በውጭም ሆነ በውስጥ ሰላም የሚያሳጡት ችግሮች አሉበት። በተለይም ለሆዳቸው ያደሩ ሕዝቡን ሰላም የሚነሱ ፤ የሚከፋፍሉና የሚገሉ ጠንቆች አሉባት።

ለእነዚህ አካላት ማስተላለፍ የምፈልገው መልእክት ለገዛ አገራቸው የሰላም ጠንቅ ከመሆን እንዲታቀቡ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ማንም እንደፈለገ እንዲከፋፍለው መፍቀድ የለበትም። በዘርና በጎሳ መከፋፈሉ የትም አያደርሰንም። አገር አልባ ትውልድ ነው የሚቀረው። ይህንን ደግሞ ከሱማሊያ መማር እንችላለን።

ለማንም የማትመች አገር ከመፍጠራችን በፊት ሁላችንም ራሳችንን መፈተሽ ነው የሚገባን። ተግባብቶ በመኖር እንጂ ሰው በመግደልና በማረድ፣ ሃብትን በማውደም የሚገኝ ትርፍ የለም።

ሌላው የመንግስት አካላት የካሮቱንና የአርጩሜውን ዘዴ መጠቀም መቻል አለባቸው። በተለይም የለውጡ ኃይሎች ለለውጡ እንቅፋት የሆኑትን አካላት ለይተው እያበጠሩ ቦታ ቦታቸውን ማስያዝ ይገባዋል። ሌላው ለወጣቱ የማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ብዙ መኖር ሲገባው ባልሆነ ቅስቀሳ ውስጥ ተሳትፎ በአጭር እንዳይቀር ራሱን መገደብና ወደ ሥራ ማተኮር አለበት።

የአገሪቱን ችግር እንደራሱ ችግር ቆጥሮ የመፍትሄ አካል መሆን ይገባዋል። ምክንያቱም ከወጣት ውጭ የተገነባ አገር ኖሮ አያውቅም። ለሚቀጥለው ትውልድ መልካም ነገር ለማውረስ መትጋት ነው ያለበት።

ትላንት የነበረውን ቆሻሻ ነገር ልንማርበት እንጂ ልንገባበት እንደማይገባ በመገንዘብ ለእድገታችን የበኩሉን ሚና መጫወት ይገባዋል የሚል መልዕክት ነው ያለኝ።

አዲስ ዘመን ጥር 01/2013

ማህሌት አብዱል

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *