በተሻሻለው ክስ መሰረት የእምነት ክህደት ቃል እንዲሰጥ ጥያቄ የቀረበላቸው እነ ጃዋር መሐመድና አስራ ስምንት ተጠርጣሪዎች ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው በጠየቁት መሰረት ፍርድ ቤት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ። ጠበቆቻቸው  ጊዜ እንዲሰጣቸው ከደንበኞቻቸው ጋር ለመምከር እንደሆነም ታውቋል። ተከሳሾችም ቢሆኑ ” በዛሬው ቀጠሮ የእምነት ክህደት ቃል ለመስጠት ዝግጁ አይደለንም” ብለዋል።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት እነ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ 18 የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠው ለመጪው ረቡዕ ጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም ነው።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት አኤጀንሲ የችሎት ውሎውን እንደዘገበው ዐቃቤ ሕግ ጥር 04 ቀን 2013 ዓ.ም ላይ በነበረው ችሎት እንዲያሻሽላቸው ከታዘዘው የክስ ማመልከቻ ውስጥ የተወሰኑትን አሻሽሎ ማቅረቡን አስታውቋል። የክስ ማመልከቻ አስተካክሎ ቢያቀርብም ተጨማሪ ማመልከቻ አቅርቧል።
ዐቃቤ ሕግ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት ያቀረበው ማመልከቻ  በእነ ጃዋር የክስ መዝገብ አምስት ክሶች በተለይም ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ይዞ መገኘት ጋር በተያያዘ አዋጁን ጠቅሶ ዋናው ክስ ላይ የጠቀሰውን የክስ ጭብጥ ፍርድ ቤቱ እንዲያሻሽል ትእዛዝ ቢሰጥም ማሻሻል እንደማይችል የተለያዩ ምክንያቶች በዝርዝር የቀረቡበት ነው።
ችሎቱም የአፍታ ጊዜ ወስዶ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበለትን ማመልከቻ መርምሯል። በመሆኑም ከጦር መሣሪያ አዋጅ ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል የሰጠው ትእዛዝ አሳማኝ መሆኑን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ ከጦር መሣሪያ ጋር ተያይዞ በተከሳሾች ላይ ያቀረበውን ክስ የማያሻሽል መሆኑን በመገንዘብ እንዲቋረጥ ትእዛዝ ሰጥቷል።
አስከትሎም ፍርድ ቤቱ የእምነት ክህደት ቃል እንዲሰጡ ተከሳሾችን ጠይቋል።  የተከሳሽ ጠበቆች ግን ተሻሽሏል የተባለውን ክስ በአግባቡ ለመረዳት ጊዜ እንደሚያስፈለግ፣ ከደንበኞች ጋር ለመመካከርም ጊዜ ስለሚያስፈልግ በዕለቱ ቃለ መሃላ መፈጸም እንደማይቻል አስታወቀዋል። “አሁን ባለንበት ሁኔታ የእምነት ክህደት ቃል ለመስጠት ያስቸግራል። ስለዚህ አጭር ቀጠሮ ይሰጠኝ” ሲሉም አመልክተዋል። ተከሳሾችም ቢሆኑ በዛሬው ቀጠሮ የእምነት ክህደት ቃል ለመስጠት ዝግጁ አለመሆናቸውን ጠበቆቻቸውን ተከትለው አስታውቀዋል።
የጠበቆቻቸውንና የተከሳሾችን ምክንያት ከግንዛቤ ያስገባው ችሎቱ የተከሳሾች ጠበቆች ከጠቀሱት ወሳኝ በሚባለው የእምነት ክህደት ቃል መስጠት ጋር በተያያዘ በቂ ዝግጅት አድርገው እንዲመጡ ለመጪው ረቡዕ ጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ እንደተሰጣቸው ከመንግስት መገናኛዎች ለመረዳት ተችሏል።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   The Forces of Evil Arrayed Against Ethiopia ( (Part I of II)-By almariam

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *