በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ጽኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር መጨመር በስራው ላይ ጫና ማሳደሩን የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል አስተወቀ የቫይረሱ ስርጭት በጌዴኦ ዞንና አጎራባች አከባቢዎች ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደር እንደሚገባ ተጠቁሟል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር በረከት ብዙነህ ለኢዜአ እንደገለጹት ሆስፒታሉ ለይቶ ማከሚያና የናሙና ምርመራን ጨምሮ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል።

በየደረጃው ባሉ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጨምሮ በህብረተሰቡ ዘንድ ቫይረሱን የመከላከልና የጥንቃቄ ተግባር ቸል መባሉን ተከትሎ የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ መጠን እየተስፋፋ መምጣቱን አስረድተዋል።

በየቀኑ በአማካይ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ከ8 ሰዎች በላይ በለይቶ ማከሚያና ከዚያም ሲያልፍ በከፍተኛ ክትትል ጽኑ ህሙማን ክፍል እየገቡ መሆኑን ለዓብነት አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት ለከፍተኛ የህክምና ክትትል ጽኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ ሆስፒታሉ መደበኛ አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል።

በጽኑ ህክምና ክፍል የህሙማኑ ቁጥር አየጨመረ በመምጣቱ ኦክስጅን ጨምሮ ለሌች የህክምና ግብዓቶች እጥረት እንዲከሰት ማድረጉን ተናግረዋል።

በሆስፒታሉ ሁለት ኢስፔሻሊስት ሃኪሞችን ጨምሮ በርካታ የጤና ባለሙያዎች በስራቸው ላይ እያሉ በቫይረሱ እንዲያዙ ምክንያት መሆኑንም አመልከተዋል ።

ሆስፒታሉ ከዚህ ቀደም ለአጠቃላይ ህክምና በየሁለት ሳምንቱ 100 ሲሊንደር ኦክስጅን ይጠቀም እንደነበር ያነሱት ዶክተር በረከት በአሁኑ ወቅት ለለይቶ ማከሚያ ክፍል ብቻ በቀን ከ15 በላይ ሲሊንደር ኦክሲጅን እየተጠቀመ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

በሆስፒታሉ በህሙኘማኑ ቁጥር መጨመር በህክምናው ላይ ከፈጠረው ጫና በተጓዳኝ  የሚመዘገበው የሞት ምጣኔን ከፍ እንዲል ማድረጉን የገለጹት ዶክተር በረከት ባለፉት አስር ቀናት ውስጥ ብቻ በቫይረሱ ምክንያት የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን አስታውቀዋል።

በጤና ተቋማት ብቻ የሚደረገው የመከላከል ስራ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚያስችል ባለመሆኑ ህብረተሰቡ እራሱንና ቤተሰቡን ከቫይረሱ መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በተለይ በፋይናንስና በማህበራዊ ተቋማት እንዲሁም በትራንፖርት አገልግሎት እየተጣሱ የሚገኙ የኮቪድ ፕሮቶኮሎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በሆስፒታሉ በሚገኝ ማዕከል በየቀኑ 90 ለሚደርሱ ናሙናዎች ምርመራ እንደሚደረግ የገለጹት ደግሞ  በሆስፒታሉ የላብራቶሪ ክፍል አስተባባሪ አቶ ጀማል ሙሉ ናቸው።

በተለይ እድሜያቸው የገፋ ሰዎች በይበልጥ ለቫይረሱ ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቁመው በአንድ ቀን ምርመራ ከተደረገላቸው 20 ሰዎች ሰባቱ ቫይረሱ የተገኘባቸው ክስተት መኖሩን አመልከተዋል ። አሁን ያለው የቫይረሱ ስርጭት እጅግ አስደንጋጭ ቢሆንም ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ ምንም አይነት ጥንቃቄ ማድረግ ማቆሙን አመለከተዋል።

የቫይረሱ ስርጭት በጌዴኦ ዞንና አጎራባች አከባቢዎች ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ ቢያንስ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በመጠቀም ጥንቃቄ ሊያደር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

(ኢዜአ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *