“Our true nationality is mankind.”H.G.

በሳሊቫኪርና በሪክ ማቻር መካከል እያገረሸ ያለውን ቅራኔ እየተባባሰ በመምጣቱ በደቡብ ሱዳን አዲስ ግጭት እንዳያገረሽ ተሰግቷል

ደቡብ ሱዳን ነጻነቷን ካገኘች ጀምሮ በእርስ በርስ ጦርነት ብዙ ዜጐቿን አጥታለች። ከብዙ ጥረት በኋላ አሁን ላይ የፕሬዚዳንትነትን እና የምክትል ፕሬዚዳንቱን መቀመጫ በያዙት በሳሊቫኪር እና ሪክ ማቻር መካከል በተፈጠረው የሰላም ስምምነት ደም አፋሳሹ ጦርነት አብቅቶ በርካታ የሃገሪቱ አካባቢዎች የተረጋጉ ሆነው ቆይተዋል።

ነገር ግን በቅርቡ እያገረሸ ያለውን የሁለቱ ባለሥልጣናት ግንኙነት እና የደጋፊዎች ቅራኔ እየተባባሰ በመምጣቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መጠነ ሰፊ የሆነ ግጭት ሊቀሰቀስ እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሪፖርት አውጥቷል።

ሪፖርቱ በሃገሪቱ የፖለቲካ፣ ወታደራዊ እና የጐሣ ቅራኔዎች እየተባባሱ መምጣታቸውን አመላክቶ ከዚህ ቀደም ተከስቶ የነበረውን አውዳሚ ጦርነት ለመግታት የተፈረመው ስምምነትን የሚጥሱ ድርጊቶችም በተደጋጋሚ እየተስተዋሉ መሆኑን ስለመታዘቡ አትቷል።

“የባለፈው ጦርነት የመመለስ አዝማሚያ አለው፤ መቶ ሺህ የሚጠጉ ዜጎችም ረሃብ መሰል ሁኔታ ገጥሟቸዋል” ሲል ሪፖርቱ የሃገሪቱን ሁኔታ አሳሳቢነት ጠቅሷል።

Related stories   Ceasing Egyptians’ false narrative about Nile breaks GERD deadlock

ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ በበኩሉም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት ብዙም ልዩነት የሌለው ሪፖርት አውጥቷል። በሪፖርቱም በሳልቫኪር የሚመራው የደቡብ ሱዳን መንግሥት ቀስ በቀስ ባደረገው ሪፎርም እና ባለፈው ዓመት የተፈረመውን የተኩስ አቁም ስምምነት አተገባበር ላይ አለመግባባቶች መከሰታቸው በሁለቱ ባለስልጣናት በኩል ያሉ ጎሳዎች መካከል ውጥረት እንዲከሰት ሆኗል።

በአስተዳደሩ ውስጥ ያለውን ውስጣዊ ውጥረት ለመቆጣጠር አለመቻሉ በሕዝቡ ዘንድ አለመተማመን እንዲባባስ ምክያንት መሆኑ ተገልጿል።

በሪክ ማቻር በኩል ያሉ ባለስልጣናት ደግሞ አስተዳደሩን በጥብቅ እየተቹ ስለመሆናቸው እናየተወሰኑትም በመንግሥት ላይ ያላቸውን እምነት እያጡ መምጣታቸው በተመሳሳይ በስፋት እየተነገረ ነው።

ዓለም አቀፉ የረሃብ አደጋ ማስጠንቀቂያ ተቋም ደግሞ በደቡብ ሱዳን በዚህ ዓመት ብቻ 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጿል። የሃገሪቱ መንግሥት ግን ይህንን ጉዳይ ከመቅረፍ ይልቅ ቢሮክራሲያዊ ሥርዓትን የማስፋፋት ሥራ ላይ ስለመጠመዱ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እየዘገቡ ነው።

የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ በዚህ ዓመት የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልገዋል። የቀጠለው አለመረጋጋት ደግሞ ይህን ተግባር የባሰ እንዲገታ አድርጎታል ማለቱን አልጀዚራ ዘግቧል።

የክራይሲስ ግሩፕ ሪፖርት የሰሩ ባለሙያዎችን ዋቢ አድርጎ አሶሺየትድ ፕሬስ እንደዘገበው ደግሞ በሃገሪቱ ሳይታረም ያለፉ ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንዲሁም ብሔራዊ አለመግባባቶች በመቀጠላቸው የሰላም ጉዳይ አሁንም በስጋት ውስጥ ያለ መሆኑን ይገልፃል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ፖለቲከኞች እንዲሁም ወታደራዊ አመራሮች በሃገሪቱ ቀጣይነት ያለው ሰላም እንዲኖር እና የሳልቫኪር እና ሪክ ማቻር ከሥልጣን እንዲወርዱ የሚጠይቁት ጥያቄ ሃገሪቱ ለተጋረጠባት መጠነ ሰፊ ግጭት ስጋት ለማስቀረት ሲባል በፍጥነት ማጤን ሊጠቅም እንደሚችልም አመልክቷል።

በፈረንጆቹ 2006 ጀምሮ እስከ ባለፈው ዓመት ድረስ ቀጥሎ በነበረው የሁለት ቡድኖች ጦርነት ከሃምሳ ሺህ የሚበልጡ ዜጎች ለሞት መዳረጋቸው ሲነገር ነበር።

በእርግጥ የሟቾች ቁጥር ከተነገረው እጅግ የላቀ ሊሆን እንደሚችልም ግምታዊ ሪፖርቶች ሲወጡ ቆይተዋል።

በወርሃ ጥቅምት በፈረንጆቹ 2011 ሪክ ማቻር ወደ ደቡብ ሱዳን በመግባት ከቀድሞው ባላንጣቸው ሳል ቫኪር ጋር የሰላም ማብሰሪያ ፕሮግራም ካካሄዱ በኋላ ነገሮች ቀስ በቀስ እየረገቡ በመሄዳቸው በሃገሪቱ ላይ የሰላም ተስፋ ታይቶ ነበር።

ለሁለት ዓመት ተኩል ገደማ አንጻራዊ መረረጋት የታየበት የደቡብ ሱዳን መንግሥት ዛሬም እንደገና ወደ ቀድሞው ውጥረት የሚመለስ ከሆነ ከባለፉት ዓመታት ያልተናነሰ የለየለት ጦርነት ውስጥ ሊገባ ስለሚችል ለሃገሪቱ ብቻም ሳይሆን በቀጠናው ላይ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችልም የዓለም አቀፍ ተቋማት ስጋታቸውን ማሰማት ቀጥለዋል።

አሁን ላይ ስላለው ሁኔታ የሃገሪቱ የዜና አውታር የሆነው የደቡብ ሱዳን ዜና አገልግሎት በቅርቡ ባወጣው ዘገባ ደግሞ ንፁሃን ዜጎች በታጣቂዎች ዒላማ እየሆኑ መምጣታቸውን እና በታጣቂዎች የሚገደሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አመልክቷል። በቅርቡ በተፈፀመ ግድያ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ንፁሃን እየተገደሉ መሆናቸውን የሰብዓዊ መብት ተቋሟትን እማኝ አድርጎ ዘግቧል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ጠቅሶ አፍሪካ ኒውስ እንደዘገበው ደግሞ የደቡብ ሱዳን መንግሥት የመዋቅር ክፍተት ከዝቅተኛ አስተዳደር እርከን እስከ ፌዴራል መንግሥት ድረስ መኖሩ ለእነዚህ ጥቃቶች መባባስ እንደ ምክንያት ያሳያል።

በሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ፀሐፊ የሆኑት ያስሚን ሶቃ ከሁለት ዓመት በፊት የተፈረመው የሰላም ስምምነት በዜጎች መካከል የነበረውን መጠላላት እንዲቀንስ አድርጎ የነበረ መሆኑን በማስታወስ አሁን ላይ በተለያዩ አካባቢዎች የግጭት ቅድመ ሁኔታዎች እየታዩ መሆናቸውን ለአፍሪካ ኒውስ ተናግረዋል።

የሱፍ እንድሪስ

አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013

Related stories   ‹‹የህዳሴው ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም አለው፤ የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስር ያጠነክራል››

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0